ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 48:13-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

13. “ከካህናቱም ምድር ጐን ለጐን ሌዋውያኑ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመትና ዐሥር ሺህ ክንድ ወርድ ያለው ይዞታ ይኖራቸዋል፤ ጠቅላላ ርዝመቱ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ፣ ወርዱም ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል።

14. ከዚህ ላይ መሸጥ ወይም መለወጥ የለባቸውም። ይህ ከምድሪቱ ሁሉ ምርጥ ስለ ሆነ፣ ወደ ሌላ እጅ አይተላለፍም፤ ለእግዚአብሔር የተቀደሰ ነውና።

15. “አምስት ሺህ ክንድ ወርድና ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ርዝመት ያለው የቀረው ቦታ ለከተማዪቱ የጋራ ጥቅም፣ ለቤት ሥራና ለከብት ማሰማሪያ ይውላል፤ ከተማዪቱም በመካከሉ ትሆናለች፤

16. የከተማዪቱም መጠን በሰሜን አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በደቡብ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ በምሥራቅ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ፣ የምዕራቡም እንዲሁ አራት ሺህ አምስት መቶ ክንድ ይሆናል።

17. የከተማዪቱ ከብት ማሰማሪያ ቦታ፣ በሰሜን ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በደቡብ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምሥራቅ ሁለት መቶ አምሳ ክንድ፣ በምዕራብም ሁለት መቶ አምሳ ክንድ ይሆናል።

18. ከዚህ የሚቀረው፣ የተቀደሰውን ክፍል የሚያዋስነውና በተጓዳኝ ያለው ቦታ በምሥራቅ ዐሥር ሺህ ክንድ፣ በምዕራብ ዐሥር ሺህ ክንድ ይሆናል። ምርቱም ለከተማዪቱ ሠራተኞች ምግብ ይሆናል።

19. ምድሪቱን የሚያርሱ የከተማዪቱ ሠራተኞች ከሁሉም ነገዶች ይመጣሉ።

20. አጠቃላይ ይዞታው በአራቱም ማእዘን እኩል ሲሆን፣ እያንዳንዱ ማእዘን ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ነው፤ ከከተማዪቱ ድርሻ ጋር የተቀደሰውን ክፍል ልዩ መባ በማድረግ ታስቀምጣላችሁ።

21. “በተቀደሰው ድርሻና በከተማዪቱ ቦታ ግራና ቀኝ ያለው ቀሪ ቦታ፣ ለገዡ ይሆናል፤ ይህም ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ከተቀደሰው ቦታ አንሥቶ በምሥራቅ በኩል እስከ ምሥራቁ ወሰን ይዘልቃል፤ በምዕራቡም በኩል እንዲሁ ሃያ አምስት ሺህ ክንድ ከሆነው ይዞታ አንሥቶ እስከ ምዕራቡ ወሰን ይዘልቃል። የየነገዱ ድርሻ ከሆነውም መሬት ጐን ለጐን የሚሄዱት ቦታዎች የገዡ ይሆናሉ። የተቀደሰው ቦታና መቅደሱ በመካከላቸው ይሆናሉ።

22. ስለዚህ የሌዋውያኑ ይዞታና የከተማዪቱ ይዞታ ለገዡ በተሰጠው ቦታ መካከል ይሆናል፤ የገዡ ቦታም በይሁዳ ድንበርና በብንያም ድንበር መካከል ይሆናል።

23. “የቀሩት ነገዶች ድርሻ እንደሚከተለው ይሆናል፤ ‘የብንያም ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ይዘልቃል።

24. “ ‘የስምዖን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

25. “ ‘የይሳኮር ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የስምዖንን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

26. “ ‘የዛብሎን ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የይሳኮርን ምድር ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

27. “ ‘የጋድ ነገድ አንድ ድርሻ ይኖረዋል፤ ይህም የዛብሎንን ግዛት ከምሥራቅ እስከ ምዕራብ ያዋስናል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 48