ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 43:11-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. ስላደረጉት ነገር ሁሉ ኀፍረት የሚሰማቸው ከሆነ፣ የቤተ መቅደሱን ንድፍ እንዲያውቁት አድርግ፤ ይኸውም አሠራሩን፣ መውጫና መግቢያውን፣ አጠቃላይ ንድፉን፣ ሥርዐቱንና ሕጉን ሁሉ ነው። ንድፉንና ሥርዐቱን እንዲጠብቁና እንዲከተሉ እነዚህን ሁሉ እነርሱ ባሉበት ጻፋቸው።

12. “የቤተ መቅደሱ ሕግ ይህ ነው፤ በተራራው ጫፍ አካባቢ ያለው ስፍራ ሁሉ እጅግ የተቀደሰ ይሆናል። የቤተ መቅደሱም ሕግ ይኸው ነው።

13. “የመሠዊያው ልክ በረጅም ክንድ ይህ ነው፤ ይኸውም ክንድ ከስንዝር ማለት ነው፤ ቦዩ አንድ ክንድ ጥልቀት፣ አንድ ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ዙሪያው አንድ ስንዝር ጠርዝ አለው፤ የመሠዊያውም ከፍታ ይህ ነው፤

14. ከቦዩ መሠረት አንሥቶ እስከታችኛው ዕርከን ድረስ ሁለት ክንድ ቁመት፣ ሁለት ክንድ ወርድ ያለው ሲሆን፣ ከትንሹ ዕርከን አንሥቶ እስከ ትልቁ ዕርከን ድረስ ደግሞ አራት ክንድ ቁመት፣ አንድ ክንድ ወርድ አለው።

15. የመሠዊያው ምድጃ ከፍታው አራት ክንድ ሲሆን፣ ከምድጃው ወጣ ወጣ ያሉ አራት ቀንዶች አሉ።

16. የመሠዊያው ምድጃ እኩል በእኩል ሲሆን፣ ርዝመቱ ዐሥራ ሁለት ክንድ፣ ወርዱም ዐሥራ ሁለት ክንድ ነው።

17. ላይኛው ዕርከንም እንዲሁ እኩል በእኩል ሆኖ ዐሥራ አራት ክንድ ርዝመትና ዐሥራ አራት ክንድ ወርድ አለው፤ ግማሽ ክንድ ጠርዝና ዙሪያውን በሙሉ አንድ ክንድ የሆነ ቦይ ነበረው። የመሠዊያው ደረጃዎችም በምሥራቅ ትይዩ ናቸው።”

18. ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ መሠዊያው ተሠርቶ፣ የሚቃጠል መሥዋዕት በሚሠዋበትና በመሠዊያው ላይ ደም በሚረጭበት ጊዜ ሥርዐቶቹ እነዚህ ናቸው፤”

19. በፊቴ ቀርበው ለሚያገለግሉኝ ካህናት፣ ለሌዋውያኑ ለሳዶቅ ቤተ ሰብ የኀጢአት መሥዋዕት የሚሆን አንድ ወይፈን ስጥ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

20. ከደሙም ጥቂት ወስደህ፣ በመሠዊያው አራት ቀንዶች፣ በላይኛው ዕርከን አራት ጐኖች ላይ እንዲሁም በጠርዙ ዙሪያ ሁሉ ታደርጋለህ፤ በዚህ ሁኔታ መሠዊያውን ታነጻለህ፤ ታስተሰርይለታለህም።

21. ወይፈኑን ስለ ኀጢአት መሥዋዕት ወስደህ፣ በቤተ መቅደሱ አካባቢ ከመቅደሱ ውጩ ለዚሁ ተብሎ በተመደበው ስፍራ ታቃጥለዋለህ።

22. “በሁለተኛው ቀን እንከን የሌለበት ተባት ፍየል ወስደህ ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለህ፤ መሠዊያው በወይፈኑ እንደ ነጻ ሁሉ፣ በዚህም መንጻት አለበት።

23. ማንጻቱን ከፈጸምህ በኋላ፣ ከመንጋው እንከን የሌለባቸውን አንድ ወይፈንና አንድ አውራ በግ ታቀርባለህ።

24. በእግዚአብሔር ፊት ታቀርባቸዋለህ፤ ካህናቱ ጨው ይነሰንሱባቸዋል፤ ለእግዚአብሔርም የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው ያቀርቧቸዋል።

25. “በየዕለቱ ለሰባት ቀን ተባት ፍየል ለኀጢአት መሥዋዕት ታቀርባለህ፤

26. ሰባት ቀን ለመሠዊያው ያስተሰርዩለታል፤ ያነጹታልም፤ እንዲህም አድርገው ይቀድሱታል።

27. እነዚህ ቀኖች ካለፉ በኋላም፣ ከስምንተኛው ቀን ጀምሮ ካህናቱ የሚቃጠለውን መሥዋዕታችሁንና የኅብረት መሥዋዕታችሁን በመሠዊያው ላይ ያቀርባሉ። ከዚያም እኔ እቀበላችኋለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 43