ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 40:17-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

17. ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።

18. የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።

19. ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።

20. ከዚያም በሰሜን ትይዩ ያለውን፣ ወደ ውጩ አደባባይ የሚያመራውን በር ርዝመትና ወርድ ለካ።

21. እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

22. መስኮቶቹ፣ መተላለፊያ በረንዳዎቹና የዘንባባ ዛፍ ቅርጾቹ ልካቸው በምሥራቁ በር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ወደዚያ የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያ በረንዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ትይዩ ነበር።

23. ልክ በምሥራቅ በኩል እንዳለው ሁሉ፣ ከሰሜኑ በር ጋር ትይዩ የሆነ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያመራ በር አለ። ከአንዱ በር እስከ ሌላኛው በር ያለውን ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ነበር።

24. ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መራኝ፤ እዚያም ፊቱን ወደ ደቡብ ያደረገ በር አየሁ፤ እርሱም የውስጠኛውን ግድግዳና መተላለፊያ በረንዳውን ለካ፤ የእነዚህም መጠን እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።

25. የመግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዙሪያው ጠባብ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፤ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

26. ከመተላለፊያ በረንዳው ትይዩ የሆኑ ሰባት ደረጃዎች ወደ መግቢያው በር ያመራሉ፤ ወጣ ወጣ ብለው በሚታዩ ግድግዳዎችም ላይ የዘንባባ ቅርጽ አለ።

27. ውስጠኛው አደባባይ ደግሞ ከደቡብ ጋር ትይዩ የሆነ በር አለው፤ እርሱም ከዚህ በር አንሥቶ በደቡብ አቅጣጫ እስካለው እስከ ውጭው በር ድረስ ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ሆነ።

28. ከዚያም በደቡብ በር በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ የደቡብንም በር ለካው፤ መጠኑም እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።

29. የዘብ ቤቶቹ፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉት ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር። መግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳዎቹ በዙሪያቸው መስኮቶች ነበሯቸው። ርዝመቱ አምሳ ክንድ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

30. በውስጠኛው አደባባይ ዙሪያ ያሉት የመግቢያው በር መተላለፊያ በረንዳዎቹ ርዝመት ሃያ አምስት ክንድ ሲሆን፣ ወርዳቸው ደግሞ አምስት ክንድ ነበር።

31. መተላለፊያ በረንዳው ከውጭው አደባባይ ጋር ትይዩ ነው፤ የዘምባባ ዛፎች በዐምዶቹ ላይ ተቀርጸዋል፤ እስከ መግቢያው ድረስም ስምንት ደረጃዎች ነበሩት።

32. ከዚያም በምሥራቅ በኩል ወደ ውስጠኛው አደባባይ አመጣኝ፤ መግቢያ በሩንም ለካው፤ መጠኑም ከሌሎቹ ጋር ተመሳሳይ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 40