ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 40:14-27 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

14. በመግቢያው በር ዙሪያ ባሉት ወጣ ወጣ ባሉት ግንቦች ሁሉ ፊት ለፊት ያለውን ቦታ ለካ፤ ሥልሳ ክንድም ነበር። የተለካውም ከአደባባዩ ፊት ለፊት እስካለው መተላለፊያ በረንዳ ድረስ ነበር።

15. ከበሩ መግቢያ እስከ መተላለፊያ በረንዳው መጨረሻ ድረስ ያለው ርቀት አምሳ ክንድ ነበር።

16. ክፍሎቹ እንደ መተላለፊያ በረንዳዎቹ ከግራና ከቀኝ በኩል ትንንሽ መስኮቶች አሏቸው። በዙሪያው ያሉ መስኮቶች በመግቢያው በር ፊት ለፊት የነበሩ ሲሆን፣ በእያንዳንዱ ክፍል ግራና ቀኝ ግድግዳ ላይ ደግሞ የዘንባባ ዛፍ ተቀርጾበታል።

17. ከዚያም ወደ ውጩ አደባባይ አመጣኝ፤ እዚያም በአደባባዩ ዙሪያ የተሠሩ ክፍሎችና ድንጋይ የተነጠፈበት መመላለሻ አየሁ፤ በመመላለሻውም ዙሪያ ሠላሳ ክፍሎች ነበሩ።

18. የታችኛው ንጣፍ ወለል ከመግቢያው በር ጋር ተያይዞ የተሠራ ሲሆን፣ ስፋቱ እንደ በሮቹ ርዝመት መጠን ነበር።

19. ከዚያም ከታችኛው መግቢያ በር ፊት ጀምሮ እስከ ውስጠኛው አደባባይ ፊት ድረስ ያለውን ርቀት ለካ፤ በምሥራቅም ሆነ በሰሜን በኩል ያለው ርቀት አንድ መቶ ክንድ ነበር።

20. ከዚያም በሰሜን ትይዩ ያለውን፣ ወደ ውጩ አደባባይ የሚያመራውን በር ርዝመትና ወርድ ለካ።

21. እንደ መጀመሪያው በር ሁሉ ይኸኛውም በየጐኑ ያሉት ሦስት ሦስት የዘብ ቤቶች፣ በየመካከሉ ወጣ ወጣ ያሉ ግንቦችና መተላለፊያ በረንዳዎቹ መጠናቸው እኩል ነበር። ርዝመቱ አምሳ ክንድ፣ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

22. መስኮቶቹ፣ መተላለፊያ በረንዳዎቹና የዘንባባ ዛፍ ቅርጾቹ ልካቸው በምሥራቁ በር ካሉት ጋር ተመሳሳይ ነበር። ወደዚያ የሚያመሩ ሰባት ደረጃዎች አሉ፤ መተላለፊያ በረንዳዎቹም ከእነርሱ ጋር ትይዩ ነበር።

23. ልክ በምሥራቅ በኩል እንዳለው ሁሉ፣ ከሰሜኑ በር ጋር ትይዩ የሆነ ወደ ውስጠኛው አደባባይ የሚያመራ በር አለ። ከአንዱ በር እስከ ሌላኛው በር ያለውን ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ነበር።

24. ከዚያም ወደ ደቡብ አቅጣጫ መራኝ፤ እዚያም ፊቱን ወደ ደቡብ ያደረገ በር አየሁ፤ እርሱም የውስጠኛውን ግድግዳና መተላለፊያ በረንዳውን ለካ፤ የእነዚህም መጠን እንደ ሌሎቹ በሮች ነበር።

25. የመግቢያው በርና መተላለፊያ በረንዳው እንደ ሌሎቹ ሁሉ በዙሪያው ጠባብ መስኮቶች ነበሩት፤ ርዝመቱ አምሳ ክንድ፤ ወርዱም ሃያ አምስት ክንድ ነበር።

26. ከመተላለፊያ በረንዳው ትይዩ የሆኑ ሰባት ደረጃዎች ወደ መግቢያው በር ያመራሉ፤ ወጣ ወጣ ብለው በሚታዩ ግድግዳዎችም ላይ የዘንባባ ቅርጽ አለ።

27. ውስጠኛው አደባባይ ደግሞ ከደቡብ ጋር ትይዩ የሆነ በር አለው፤ እርሱም ከዚህ በር አንሥቶ በደቡብ አቅጣጫ እስካለው እስከ ውጭው በር ድረስ ለካው፤ ይህም አንድ መቶ ክንድ ሆነ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 40