ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 39:16-28 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. በዚያም ሐሞና የምትባል ከተማ አለች፤ ስለዚህ ምድሯን ያጸዳሉ።’

17. “ ‘የሰው ልጅ ሆይ፤ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘ማንኛውንም ዐይነት ወፍና የዱር አራዊት ሁሉ ጥራ፤ እንዲህም በላቸው፤ “ከየአቅጣጫው ተሰብስባችሁ እኔ ወደማዘጋጅላችሁ መሥዋዕት ኑ፤ ይህም በእስራኤል ተራሮች ላይ የሚሆን ታላቁ መሥዋዕት ነው። በዚያ ሥጋ ትበላላችሁ፤ ደምም ትጠጣላችሁ።

18. እንደ አውራ በግና እንደ ጠቦት፤ እንደ ፍየልና እንደ ወይፈን፣ የኀያላን ሰዎችን ሥጋ ትበላላችሁ፤ የምድርንም መሳፍንት ደም ትጠጣላችሁ፤ እነዚህ ሁሉ የሰቡ የባሳን ከብቶች ናቸው።

19. እኔ በማዘጋጅላችሁም መሥዋዕት እስክትጠግቡ ስብ ትበላላችሁ፤ እስክትሰክሩም ደም ትጠጣላችሁ።

20. በገበታዬም ፈረሶችንና ፈረሰኞችን፣ ኀያላን ሰዎችንና ከየወገኑ የሆኑትን ወታደሮች እስክትጠግቡ ትበላላችሁ፤” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

21. “ክብሬን በአሕዛብ መካከል እገልጣለሁ፤ አሕዛብም ሁሉ በእነርሱ ላይ ያመጣሁትን ቅጣትና በላያቸው ላይ የጫንሁትን እጅ ያያሉ።

22. ከዚያን ጊዜ ጀምሮ የእስራኤል ቤት እኔ እግዚአብሔር፣ አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።

23. አሕዛብም የእስራኤል ሕዝብ ለእኔ ታማኞች ባለመሆን ከሠሩት ኀጢአት የተነሣ እንደ ተሰደዱ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ፊቴን ከእነርሱ ሰወርሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ ሰጠኋቸው፤ ሁሉም በሰይፍ ወደቁ።

24. እንደ ርኵሰታቸውና እንደ በደላቸው መጠን ፈረድሁባቸው፤ ፊቴንም ከእነርሱ ሰወርሁ።

25. “ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ያዕቆብን አሁን ከስደት እመልሰዋለሁ፤ ለእስራኤል ሕዝብ ሁሉ እራራለሁ፤ ስለ ቅዱስ ስሜም እቀናለሁ።

26. የሚያስፈራቸው ማንም ሳይኖር በምድራቸው በሰላም በሚኖሩበት ጊዜ፣ ውርደታቸውንና ለእኔ ታማኝ ሆነው ያልኖሩበትን ዘመን ይረሳሉ።

27. ከአሕዛብ ምድር መልሼ ሳመጣቸው፣ ከጠላቶቻቸው አገር ስሰበስባቸው የራሴን ቅድስና በእነርሱ በኩል በብዙ ሕዝቦች ፊት አሳያለሁ።

28. በአሕዛብ መካከል እንዲሰደዱ ባደርግም፣ አንድም ሳላስቀር ወደ ገዛ ምድራቸው እመልሳቸዋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እንደሆንሁ ያውቃሉ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 39