ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 37:1-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም በእግዚአብሔር መንፈስ አወጣኝ፤ በሸለቆ መካከልም አኖረኝ፤ ሸለቆውም በዐጥንቶች ተሞልቶ ነበር።

2. በእነርሱም መካከል ወደ ፊትና ወደ ኋላ አመላለሰኝ፤ በሸለቆውም ወለል ላይ በጣም የደረቁ እጅግ ብዙ ዐጥንቶች አየሁ።

3. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እነዚህ ዐጥንቶች በሕይወት ሊኖሩ ይችላሉን?” ሲል ጠየቀኝ።እኔም፣ “ጌታ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ ብቻ ታውቃለህ” አልሁ።

4. ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “ለእነዚህ ዐጥንቶች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘እናንት ደረቅ ዐጥንቶች፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ!

5. ጌታ እግዚአብሔር ለእነዚህ፤ ዐጥንቶች እንዲህ ይላል፤ “እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ እናንተም በሕይወት ትኖራላችሁ።

6. ጅማት አደርግላችኋለሁ፤ ሥጋ አለብሳችኋለሁ፤ በቆዳ እሸፍናችኋለሁ፤ በውስጣችሁም እስትንፋስ አገባባችኋለሁ፤ በሕይወት ትኖራላችሁ፤ እኔም እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።” ’

7. ስለዚህ እንደ ታዘዝሁት ትንቢት ተናገርሁ፤ ትንቢቱን በምናገርበትም ጊዜ የኵሽ ኵሽታ ድምፅ ተሰማ፤ ዐጥንቶቹም አንድ ላይ ሆኑ፤ ዐጥንት ከዐጥንት ጋር ተጋጠመ።

8. እኔም ተመለከትሁ፤ ጅማት ነበረባቸው፤ ሥጋም በላያቸው ታየ፤ ቆዳም ሸፍኖአቸዋል፤ እስትንፋስ ግን በውስጣቸው አልነበረም።

9. ከዚያም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለነፋሱ ትንቢት ተናገር፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በለው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ነፋስ ሆይ፤ ከአራቱ ነፋሳት ዘንድ ና፤ በሕይወት እንዲኖሩም በእነዚህ በተገደሉት ላይ እፍ በልባቸው።” ’

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 37