ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 36:29-38 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ከርኵሰታችሁ ሁሉ አድናችኋለሁ፤ እህሉን እጠራለሁ፤ አበዛዋለሁም፤ ራብንም አላመጣባችሁም።

30. ከራብ የተነሣ በአሕዛብ መካከል በውርደት እንዳትሳቀቁ፣ የዛፉን ፍሬና የዕርሻውን ሰብል አበዛለሁ።

31. ከዚያም ክፉ መንገዳችሁንና የረከሰ ሥራችሁን ታስታውሳላችሁ፤ ስለ ኀጢአታችሁና ስለ አስጸያፊ ድርጊታችሁ ራሳችሁን ትጠላላችሁ።

32. ለእናንተ ስል ይህን እንደማላደርግ እንድታውቁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ በአድራጎታችሁ ዕፈሩ፤ ተሸማቀቁ!

33. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከኀጢአታችሁ ሁሉ በማነጻችሁ ቀን፣ ከተሞቻችሁ እንደ ገና መኖሪያ ይሆናሉ። የፈረሱትም እንደ ገና ይታደሳሉ።

34. በዐላፊ አግዳሚው ዐይን ጠፍ ሆኖ ይታይ የነበረው፣ ባድማ መሬት ይታረሳል።

35. እነርሱም፣ “ጠፍ የነበረው ይህ ምድር እንደ ዔድን ገነት መሰለ፤ የተደመሰሱ፣ የፈራረሱና ባድማ የሆኑት ከተሞች አሁን መኖሪያና ምሽግ ሆነዋል” ይላሉ።

36. ከዚያም በዙሪያችሁ የነበሩ የቀሩት አሕዛብ ፈርሶ የነበረውን መልሼ የሠራሁ፣ ጠፍ የነበረውን ያለመለምሁ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ። እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ፤ እኔም አደርገዋለሁ።”

37. “ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘እንደ ገና ለእስራኤል ቤት ልመና እሺ እላለሁ፤ ይህንም አደርግላቸዋለሁ፤ ሕዝባቸውን እንደ በግ መንጋ አበዛዋለሁ፤

38. በኢየሩሳሌም በዓላት ላይ እንደሚገኘው የመሥዋዕት በግ መንጋ አበዛዋለሁ። እነሆ! ፈራርሰው የነበሩት ከተሞች የብዙ ሕዝብ መኖሪያ ይሆናሉ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 36