ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 36:2-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠላት ስለ አንቺ፣ ‘እሰይ! እነዚያ የጥንት ተራሮች የእኛ ርስት ሆነዋል’ ብሎአል።” ’

3. ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከየአቅጣጫው ከበው በመውጋት ስላጠቋችሁ፣ ለቀሩት ሕዝቦች ሁሉ ርስት ሆናችሁ፤ ለሕዝብም መሣቂያና መሣለቂያ ሆናችሁ።”

4. ስለዚህ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች፣ ለፈራረሱ ባድማዎችና፣ በሌሎቹ በዙሪያችሁ ባሉት ሕዝቦች ተዘርፈውና መዘባበቻ ሆነው መና ለቀሩት ከተሞች እንዲህ ይላል፤

5. ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሚቃጠል ቅናቴ በቀሩት ሕዝቦች ሁሉና በኤዶም ሁሉ ላይ ተናግሬአለሁ፤ ከልብ በመነጨ ደስታና በንቀት ተሞልተው የግጦሽ መሬቴን ይዘው ይበዘብዙት ዘንድ የራሳቸው ርስት አድርገውታልና።”

6. ስለዚህ የእስራኤልን ምድር የሚመለከት ትንቢት ተናገር፤ ለተራሮች፣ ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕዝቦች ዘለፋ ስለ ተሠቃያችሁ ቍጣ በተሞላ ቅናቴ እናገራለሁ።”

7. ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እጄን አንሥቼ እምላለሁ፤ በዙሪያችሁ ያሉ ሕዝቦች ዘለፋ ይወርድባቸዋል።”

8. “ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፣ እናንተ ግን፤ ለሕዝቤ ለእስራኤል ቅርንጫፍ ታወጣላችሁ፤ ፍሬም ታፈራላችሁ፤ በቅርቡ ወደ አገራቸው ይመለሳሉና።

9. ስለ እናንተ ይገደኛል፤ በበጎነትም እመለከታችኋለሁ፤ ትታረሳላችሁ፤ ዘርም ይዘራባችኋል።

10. መላው የእስራኤል ቤት እንኳ ሳትቀሩ፣ የሰዎችን ቍጥር በእናንተ ላይ አበዛለሁ። ከተሞች የሰው መኖሪያ ይሆናሉ፤ የፈረሱት እንደ ገና ይሠራሉ።

11. በእናንተ ላይ የሰዎችንና የእንስሳትን ቍጥር እጨምራለሁ፤ ፍሬያማ ይሆናሉ፤ ቍጥራቸውም ይበዛል። እንዳለፈው ጊዜ ሁሉ ሰዎች በውስጣችሁ እንዲኖሩ አደርጋለሁ፤ ካለፈው የበለጠ አበለጽጋችኋለሁ፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።

12. ሰዎችን፣ ሕዝቤን እስራኤልን በእናንተ ላይ እንዲመላለሱ አደርጋለሁ፤ ይወርሷችኋል፤ እናንተም ርስታቸው ትሆናላችሁ፤ ከእንግዲህ ወዲህ ልጅ አልባ አታደርጓቸውም።

13. “ ‘ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ሕዝቡ እናንተን፣ ‘ሰዎችን ቦጫጭቀው ይበላሉ፤ ሕዝብንም ልጅ አልባ ያደርጋሉ’ ስላሏችሁ፣

14. ከእንግዲህ ሰው አትበሉም፤ ሕዝቡንም ልጅ አልባ አታደርጉትም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15. ከእንግዲህ የሕዝቦችን ዘለፋ እንድትሰሙ አላደርግም፤ በሰዎችም ስድብ አትሠቃዩም፤ ከእንግዲህ ለሕዝባችሁ መሰናክል አትሆኑም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

16. እንደ ገና የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 36