ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 36:1-6 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ተራሮች ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ።

2. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ጠላት ስለ አንቺ፣ ‘እሰይ! እነዚያ የጥንት ተራሮች የእኛ ርስት ሆነዋል’ ብሎአል።” ’

3. ስለዚህ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “ከየአቅጣጫው ከበው በመውጋት ስላጠቋችሁ፣ ለቀሩት ሕዝቦች ሁሉ ርስት ሆናችሁ፤ ለሕዝብም መሣቂያና መሣለቂያ ሆናችሁ።”

4. ስለዚህ የእስራኤል ተራሮች ሆይ፤ የጌታ እግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ ጌታ እግዚአብሔር ለተራሮችና ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች፣ ለፈራረሱ ባድማዎችና፣ በሌሎቹ በዙሪያችሁ ባሉት ሕዝቦች ተዘርፈውና መዘባበቻ ሆነው መና ለቀሩት ከተሞች እንዲህ ይላል፤

5. ልዑል እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሚቃጠል ቅናቴ በቀሩት ሕዝቦች ሁሉና በኤዶም ሁሉ ላይ ተናግሬአለሁ፤ ከልብ በመነጨ ደስታና በንቀት ተሞልተው የግጦሽ መሬቴን ይዘው ይበዘብዙት ዘንድ የራሳቸው ርስት አድርገውታልና።”

6. ስለዚህ የእስራኤልን ምድር የሚመለከት ትንቢት ተናገር፤ ለተራሮች፣ ለኰረብቶች፣ ለሸለቆዎችና ለውሃ መውረጃዎች እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “በሕዝቦች ዘለፋ ስለ ተሠቃያችሁ ቍጣ በተሞላ ቅናቴ እናገራለሁ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 36