ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 34:24-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

24. እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው እሆናለሁ፤ ባሪያዬ ዳዊትም በመካከላቸው ገዥ ይሆናል፤ እኔ እግዚአብሔር ተናግሬአለሁ።”

25. “ ‘ከእነርሱ ጋር የሰላም ቃል ኪዳን እገባለሁ፤ ከዚያም ምድሪቱን ከዱር አራዊት ነጻ አደርጋለሁ፤ እነርሱም በምድረ በዳ ይኖራሉ፤ በደንም ውስጥ በሰላም ይተኛሉ።

26. እነርሱንና በኰረብታዬ ዙሪያ ያሉትን ስፍራዎች እባርካለሁ። በወቅቱም ዝናብ አወርድላቸዋለሁ፤ ዝናቡም የበረከት ዝናብ ይሆናል።

27. የየሜዳው ዛፍ ፍሬ ይሰጣል፤ መሬቱም እህል ያበቅላል። ሕዝቡም በምድሪቱ ላይ በሰላም ይኖራሉ። የቀንበሮቻቸውን ማነቆ ሰብሬ በባርነት ከገዟቸው እጅ ሳድናቸው፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።

28. ከእንግዲህ ለሌሎች ሕዝቦች ንጥቂያ አይዳረጉም፤ የዱር አራዊት አይቦጫጭቋቸውም፤ በሰላም ይኖራሉ፤ የሚያስፈራቸውም አይኖርም።

29. ከእንግዲህ በምድሪቱ ላይ የራብ ተጠቂ እንዳይሆኑ፣ የአሕዛብንም ስድብ እንዳይሸከሙ ፍሬ በመስጠት የታወቀውን መሬት እሰጣቸዋለሁ።

30. ከዚያም እኔ እግዚአብሔር አምላካቸው ከእነርሱ ጋር እንደሆንሁ፤ የእስራኤል ቤት የሆኑት እነርሱም ሕዝቤ እንደሆኑ ያውቃሉ፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

31. እናንተ በጎቼ የማሰማሪያዬ በጎች ያልኋችሁ፣ ሕዝብ ናችሁ፤ እኔም አምላካችሁ ነኝ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 34