ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 33:3-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

3. እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ቢነፋ፣

4. ከዚያም ማንም መለከቱን ሰምቶ ባይጠነቀቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።

5. የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር።

6. ነገር ግን ጒበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጒበኛውን ግን ስለ ሰውዬው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’

7. “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጒበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው።

8. ክፉውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።

9. ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።

10. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት እንዲህ በል፤ ‘እንዲህ ትላላችሁ፤ “በደላችንና ኀጢአታችን ከብዶናል፤ ከዚህም የተነሣ ልንጠፋ ነው፤ ታዲያ እንዴት መኖር እንችላለን?’

11. እንዲህ በላቸው፤ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከመንገዳቸው ተመልሰው በሕይወት እንዲኖሩ እንጂ በክፉዎች ሞት ደስ አልሰኝም። ተመለሱ ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?’

12. “አሁንም የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች እንዲህ በላቸው፤ ‘ጻድቅ ሰው ትእዛዝን በተላለፈ ጊዜ የቀድሞ ጽድቁ አያድነውም፤ ኀጢአተኛ ሰው ከኀጢአቱ ከተመለሰ፣ ከቀድሞ ክፋቱ የተነሣ አይጠፋም። ጻድቅ ሰው ኀጢአት ቢሠራ፣ በቀድሞ ጽድቁ ምክንያት በሕይወት እንዲኖር አይደረግም።’

13. ጻድቁን ሰው በእርግጥ በሕይወት ትኖራለህ ብለው፣ እርሱም ጽድቁን ተማምኖ ክፋት ቢሠራ፣ ከጽድቅ ሥራው አንዱም አይታሰብለትም፤ በኀጢአቱም ምክንያት ይሞታል።

14. እንዲሁም ክፉውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ብለው፣ እርሱም ከኀጢአቱ ተመልሶ ቀና የሆነውንና ትክክለኛውንም ነገር ቢያደርግ፣

15. ለሰጠው ብድር የተቀበለውን መያዣ ቢመልስ፣ የሰረቀውንም መልሶ ቢሰጥ፣ ሕይወት የሚሰጡትን ትእዛዛት ቢከተል፣ ክፉ ነገርንም ባያደርግ፣ በእርግጥ እርሱ በሕይወት ይኖራል፤ አይሞትምም።

16. ከሠራው ኀጢአት አንዱም አይታሰብበትም፤ ቀናውንና ትክክለኛውን አድርጓልና፤ በእርግጥ በሕይወት ይኖራል።

17. “ይህም ሆኖ የአገርህ ሰዎች፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላሉ፤ ቀና ያልሆነው ግን የእነርሱ መንገድ ነው።

18. ጻድቅ ሰው የጽድቁን ሥራ ትቶ ክፉ ነገር ቢያደርግ፣ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል።

19. ክፉም ሰው ከክፉ ሥራው ተመልሶ ቀናውንና ትክክለኛውን ነገር ቢያደርግ፣ ይህን በማድረጉ በሕይወት ይኖራል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 33