ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 33:23-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

23. ከዚያም የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

24. “የሰው ልጅ ሆይ፤ በእስራኤል ምድር በፍርስራሾች ውስጥ የሚኖሩት ሕዝቦች፣ ‘አብርሃም አንድ ራሱን ብቻ ነበር፤ ያም ሆኖ ምድሪቱን ወረሰ፤ እኛ ግን ብዙዎች ነን፤ በእርግጥ ምድሪቱ ርስት ሆና ተሰጥታናለች’ ይላሉ።

25. ስለዚህ እንዲህ በላቸው፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሥጋውን ከነደሙ ትበላላችሁ፤ ዐይኖቻችሁንም ወደ ጣዖቶቻችሁ ታነሣላችሁ፤ ደምም ታፈሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ታስባላችሁ?

26. በሰይፋችሁ ትመካላችሁ፤ አስጸያፊ ነገሮችን ትፈጽማላችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የባልንጀራችሁን ሚስት ታረክሳላችሁ፤ ታዲያ በዚህ ሁኔታ ምድሪቱን ልትወርሱ ይገባችኋል?’

27. “እንዲህ በላቸው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ፤ በፍርስራሾች ውስጥ የተረፉት በሰይፍ ይወድቃሉ፤ በገጠር ያሉትን ቦጫጭቀው እንዲበሏቸው ለዱር አራዊት እሰጣቸዋለሁ፤ በምሽግና በዋሻ ያሉትም በቸነፈር ይሞታሉ።

28. ምድሪቱን ጠፍና ባድማ አደርጋታለሁ፤ የምትመካበት ጒልበቷ እንዳልነበረ ይሆናል፤ የእስራኤልም ተራሮች ማንም እንዳያልፍባቸው ባድማ ይሆናሉ።

29. ካደረጓቸው አስጸያፊ ነገሮች ሁሉ የተነሣ፤ ምድሪቱን ጠፍና ባድማ በማደርግበት ጊዜ፣ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’

30. “አንተን በሚመለከት፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ የአገርህ ሰዎች በየቤቱ በርና ግድግዳ ሥር ሆነው ስለ አንተ ይነጋገራሉ፤ እርስ በራሳቸውም እንዲህ ይባባላሉ፤ ‘ኑና ከእግዚአብሔር የመጣውን መልእክት እንስማ።’

31. ሁል ጊዜ እንደሚያደርጉት ሕዝቤ ወደ አንተ ይመጣሉ፤ ቃልህንም ለመስማት ከፊትህ ይቀመጣሉ፤ ነገር ግን አይፈጽሙትም። በከንፈራቸው ብዙ ፍቅርን ይገልጣሉ፤ ልባቸው ያረፈው ግን ተገቢ ባልሆነ ጥቅም ላይ ነው።

32. ቃልህን ሰምተው ሥራ ላይ የማያውሉት በመሆናቸው፣ አንተ ለእነርሱ በአማረ ድምፅ የፍቅር ዘፈን የሚዘፍን፣ በዜማ መሣሪያም አሳምሮ የሚጫወት ሙዚቀኛ ሆነህላቸዋል።

33. “ይህ ሁሉ ሲሆን፣ ደግሞም በርግጥ ይሆናል፣ በመካከላቸው ነቢይ እንደ ነበረ፣ ያውቃሉ።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 33