ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 33:2-9 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለአገርህ ሰዎች ተናገር፤ እንዲህም በላቸው፤ ‘በምድር ላይ ሰይፍን ሳመጣ፣ የምድሪቱ ሕዝብ ከሰዎቻቸው አንዱን መርጠው ጒበኛ ቢያደርጉት፣

3. እርሱም በምድሪቷ ላይ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ቢነፋ፣

4. ከዚያም ማንም መለከቱን ሰምቶ ባይጠነቀቅ፣ ሰይፍም መጥቶ ሕይወቱን ቢያጠፋ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል።

5. የመለከቱን ድምፅ ሰምቶ ባለመጠንቀቁ፣ ደሙ በገዛ ራሱ ላይ ይሆናል፤ ቢጠነቀቅ ኖሮ ግን ራሱን ባዳነ ነበር።

6. ነገር ግን ጒበኛ ሰይፍ ሲመጣ አይቶ፣ ሕዝቡን ለማስጠንቀቅ መለከት ሳይነፋ ቢቀርና ከመካከላቸው የአንዱን ሰው ሕይወት ሰይፍ ቢያጠፋ፣ ያ ሰው ስለ ኀጢአቱ ይወሰዳል፤ ጒበኛውን ግን ስለ ሰውዬው ደም ተጠያቂ አደርገዋለሁ።’

7. “የሰው ልጅ ሆይ፤ አንተን ለእስራኤል ቤት ጒበኛ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ የምናገረውን ቃል ስማ፤ ማስጠንቀቂያዬንም ስጣቸው።

8. ክፉውን፣ ‘አንተ ክፉ ሰው፤ በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ፣ እርሱን ከመንገዱ እንዲመለስ ባታደርገው፣ ያ ክፉ ሰው በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ስለ ደሙ ተጠያቂ ትሆናለህ።

9. ነገር ግን ክፉውን ሰው ከመንገዱ እንዲመለስ ነግረኸው እሺ ባይል፣ እርሱ ስለ ኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ራስህን አድነሃል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 33