ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 3:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ከዚያም በኮቦር ወንዝ አጠገብ በቴልአቢብ ወደሚኖሩት ምርኮኞች መጣሁ፣ በድንጋጤ ፈዝዤም ከእነርሱ ጋር ሰባት ቀን በመካከላቸው ተቀመጥሁ።

16. ከሰባቱም ቀን በኋላ የእግዚአብሔር ቃል ወደ እኔ እንዲህ ሲል መጣ፤

17. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ለእስራኤል ቤት ጠባቂ አድርጌሃለሁ፤ ስለዚህ ቃሌን ስማ፤ የምነግርህንም ማስጠንቀቂያ አስተላልፍላቸው።

18. እኔ ኀጢአተኛውን ሰው፣ ‘በእርግጥ ትሞታለህ’ ባልሁት ጊዜ አንተ ባታስጠነቅቀው፣ ነፍሱንም ያድን ዘንድ ከክፉ ሥራው እንዲመለስ ባትነግረው፣ ያ ኀጢአተኛ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።

19. ነገር ግን ኀጢአተኛውን ሰው አስጠንቅቀኸው፣ ከኀጢአቱና ከክፉ መንገዱ ባይመለስ፣ እርሱ በኀጢአቱ ይሞታል፤ አንተ ግን ነፍስህን ታድናለህ።

20. “ጻድቁ ሰው ደግሞ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ እኔም መሰናክል በፊቱ ባስቀምጥ እርሱ ይሞታል፤ አንተ አላስጠነ ቀቅኸውምና በኀጢአቱ ይሞታል፤ ያደረገውም ጽድቅ አይታሰብለትም፤ አንተንም ስለ ደሙ በኀላፊነት እጠይቅሃለሁ።

21. ነገር ግን ጻድቁን ሰው ኀጢአት እንዳይሠራ ብታስጠነቅቀውና እርሱም ኀጢአትን ባይሠራ፣ ተጠንቅቆአልና በእርግጥ በሕይወት ይኖራል፤ አንተም ነፍስህን ታድናለህ።”

22. የእግዚአብሔር እጅ በላዬ ነበረ፤ እርሱም፣ “ተነሥተህ ወደ ረባዳው ስፍራ ሂድ፤ በዚያ እናገርሃለሁ” አለኝ።

23. እኔም ተነሥቼ ወደ ረባዳው ስፍራ ሄድሁ። በኮቦር ወንዝ አጠገብ ያየሁት ዐይነት ክብር፣ የእግዚአብሔር ክብር በዚያ ቆሞ ነበር፤ እኔም በግንባሬ ተደፋሁ።

24. መንፈስ በውስጤ ገብቶ በእግሬ አቆመኝ፤ እንዲህም ሲል ተናገረኝ፤ “ሂድ፤ ቤትህ ገብተህ በርህን ዝጋ።

25. አንተ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ በገመድ ይጠፍሩሃል፤ ወጥተህም በሕዝብ መካከል እንዳትመላለስ ያስሩሃል።

26. ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም ልትገሥጻቸው እንዳትችል ምላስህን ከላንቃህ ጋር አጣብቃለሁ፤ ድዳም ትሆናለህ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 3