ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 3:1-13 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ በፊትህ ያለውን ብላ፤ ይህን ጥቅልል መጽሐፍ ብላና ሄደህ ለእስራኤል ቤት ተናገር” አለኝ።

2. ስለዚህ አፌን ከፈትሁ፤ እርሱም መጽሐፉን አጐረሠኝ።

3. እርሱም፣ “የሰው ልጅ ሆይ፤ እኔ የምሰጥህን ይህን ጥቅል መጽሐፍ ብላ፤ ሆድህንም ሙላ” አለኝ። እኔም በላሁት፤ በአፌም ውስጥ እንደ ማር ጣፈጠኝ።

4. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ ተነሥተህ ወደ እስራኤል ቤት ሂድ፤ ቃሌንም ንገራቸው።

5. ወደ እስራኤል ቤት እንጂ፣ ንግግሩ ወደማይገባና ቋንቋው ወደማይታወቅ ሕዝብ አልተላክህም፤

6. ንግግራቸው ወደማይገባና ቋንቋቸው ወደማይታወቅ፣ ቃላቸውንም መረዳት ወደማይቻልህ ብዙ ሕዝብ አልላክሁህም። ወደ እነርሱ ልኬህ ቢሆን ኖሮ፣ በእርግጥ ይሰሙህ ነበር።

7. ነገር ግን የእስራኤል ቤት ሁሉ ልበ ደንዳኖችና እልኸኞች ስለሆኑ ሊሰሙኝ አልፈለጉም፤ ስለዚህ የእስራኤል ቤት አንተንም አይሰሙህም።

8. እነሆ እኔ በእነርሱ ፊት የማትበገር ጠንካራ አደርግሃለሁ።

9. ግንባርህን ከባልጩት ይልቅ እንደሚጠነክር ድንጋይ አደርገዋለሁ። ዐመፀኛ ቤት ቢሆኑም እንኳ አትፍራቸው፤ በፊታቸውም አትሸበር።”

10. እርሱም እንዲህ አለኝ፤ “የሰው ልጅ ሆይ፤ የምነግርህን ቃል ሁሉ በጥንቃቄ አድምጥ፤ በልብህም ያዝ።

11. ተነሥተህም በምርኮ ወዳሉት ወገኖችህ ሄደህ ተናገራቸው፤ ቢሰሙህም ባይሰሙህም፣ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል’ በላቸው።”

12. መንፈስም ወደ ላይ ከፍ አድርጎ አነሣኝ፤ ከኋላዬም ‘የእግዚአብሔር ክብር በማደሪያ ስፍራው ይባረክ!’ የሚል ታላቅ ህምህምታ ሰማሁ፤

13. ይህም የሕያዋኑ ፍጡራን ክንፎች እርስ በርስ ሲጋጩና በአጠገባቸው ያሉት መንኰራኲሮች የሚያሰሙት ታላቅ ህምህምታ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 3