ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 29:5-17 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

5. አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣በምድረ በዳ እጥላለሁ።በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም።ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

6. ከዚያም በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።“ ‘ለእስራኤል ቤት የሸምበቆ በትር ነበርህ፤

7. በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ።

8. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ።

9. ግብፅ ባድማና ምድረ በዳ ትሆናለች፤ ከዚያም እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።“ ‘የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ እኔም ሠርቼዋለሁ” ብለሃልና፤

10. ስለዚህ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ፤ በወንዞችህ ላይ ተነሥቻለሁ፤ የግብፅንም ምድር ከሚግዶል እስከ አስዋን ከዚያም እስከ ኢትዮጵያ ወሰን ድረስ ፍርስራሽና ባድማ አደርጋታለሁ።

11. የሰው እግርም ሆነ የእንስሳ ኮቴ በውስጧ አያልፍም፤ እስከ አርባ ዓመት ማንም አይኖርባትም።

12. የግብፅን ምድር ከጠፉት ምድሮች መካከል እንደ አንዱ ባድማ አደርጋታለሁ፤ ከተሞቿም በፈራረሱት ከተሞች መካከል አርባ ዓመት ባድማ ይሆናሉ፤ ግብፃውያንንም በአሕዛብ መካከል እበትናቸዋለሁ፤ በአገሮችም መካከል እዘራቸዋለሁ።

13. “ ‘ያም ሆኖ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ከአርባ ዓመት በኋላ ግብፃውያንን ከተበተኑበት አገሮች መካከል እሰበስባቸዋለሁ።

14. ከተማረኩበት አመጣቸዋለሁ፤ ወደ አባቶቻቸው ምድር ወደ ጳትሮስ እመልሳቸዋለሁ።

15. ከመንግሥታት ሁሉ አነስተኛ ትሆናለች፤ ከሌሎችም አሕዛብ በላይ ራሷን ከፍ ማድረግ አትችልም። እጅግ ደካማ አደርጋታለሁ፤ ስለዚህ ሌሎችን አሕዛብ እንደ ገና መግዛት አትችልም።

16. ግብፅ ከእንግዲህ ለእስራኤል ሕዝብ መታመኛ አትሆንም፤ ለርዳታ ወደ እርሷ ዘወር ባሉ ጊዜ ላደረጉት ኀጢአት ግን መታሰቢያ ትሆናለች። ከዚያም እኔ ጌታ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።’ ”

17. በሃያ ሰባተኛው ዓመት፣ በመጀመሪያው ወር፣ በመጀመሪያው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 29