ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 29:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. በዐሥረኛው ዓመት፣ በዐሥረኛው ወር፣ በዐሥራ ሁለተኛው ቀን የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ፈርዖን አዙር፤ በእርሱና በግብፅ ሁሉ ላይ ትንቢት ተናገር፤

3. እንዲህም ብለህ ተናገረው፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል።“ ‘በወንዞችህ መካከል የምትተኛ አንተ ታላቅ አውሬ፣የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን፤ በአንተ ላይ ተነሥቻለሁ።“የዐባይ ወንዝ የእኔ ነው፤ለራሴም ሠርቼዋለሁ” ትላለህ።

4. ነገር ግን በመንጋጋህ መንጠቆ አስገባለሁ፤የወንዞችህን ዓሦች ከቅርፊትህ ጋር አጣብቃለሁ፤ቅርፊትህ ላይ ከተጣበቁት ዓሦች ሁሉ ጋር፣ከወንዞችህ ጐትቼ አወጣሃለሁ።

5. አንተንና በወንዞችህ ያለውን ዓሣ ሁሉ፣በምድረ በዳ እጥላለሁ።በገላጣ መሬት ላይ ትወድቃለህ፤የሚሰበስብህ፣ የሚያነሣህም አይኖርም።ለምድር አራዊትና ለሰማይ ወፎች፣ምግብ እንድትሆን አሳልፌ እሰጥሃለሁ።

6. ከዚያም በግብፅ የሚኖሩ ሁሉ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።“ ‘ለእስራኤል ቤት የሸምበቆ በትር ነበርህ፤

7. በእጃቸው ሲይዙህ ተሰንጥረህ ትከሻቸውን ወጋህ፤ ሲደገፉህም ተሰብረህ ጀርባቸውን አጐበጥህ።

8. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሰይፍ አመጣብሃለሁ፤ ሰዎችህንና እንስሶቻቸውን እገድላለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 29