ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 21:1-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

2. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ፊትህን ወደ ኢየሩሳሌም አዙር፤ በመቅደሱ ላይ ቃል ተናገር፤ በእስራኤል ምድር ላይ ትንቢት ተንብይ፤

3. እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ እኔ በአንቺ ላይ ተነሥቻለሁ፤ ሰይፌን ከሰገባው እመዛለሁ፤ ጻድቁንም፣ ክፉውንም ከአንተ ዘንድ አስወግዳለሁ።

4. ጻድቁንም ክፉውንም ስለማስወ ግድ ሰይፌ ከደቡብ ጀምሮ እስከ ሰሜን ባለው ሕዝብ ሁሉ ላይ ከሰገባው ይመዘዛል።

5. ሰይፌን ከሰገባው የመዘዝሁት እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ሕዝቡ ሁሉ ያውቃል፤ እርሱም ወደ ሰገባው አይመለስም።’

6. “ስለዚህ የሰው ልጅ ሆይ፤ አቃስት፤ በተሰበረ ልብና በመረረ ሐዘን አቃስት፤

7. እነርሱም፣ ‘ለምን ታቃስታለህ?’ ቢሉህ፣ “ስለሚመጣው ክፉ ወሬ ነው፤ ልብ ሁሉ ይቀልጣል፤ እጅም ሁሉ ይዝላል፤ ነፍስ ሁሉ ይደክማል፤ ጒልበትም ሁሉ ውሃ ይሆናል’ በላቸው። እነሆ ይመጣል፤ ይፈጸማልም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።”

8. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

9. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤ እንዲህም በል፤ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤“ሰይፍ! ሰይፍ!የተሳለ የተወለወለም፤

10. የተሳለው ሊገድል፣የተወለወለውም እንደ መብረቅ ሊብረቀረቅ ነው!“ ‘ታዲያ፣ እንዴት ደስ ሊለን ይችላል? ሰይፉ የልጄን በትረ መንግሥት እንደ ማንኛውም በትር ንቆአል።

11. “ ‘በእጁ እንዲያዝ፣ሰይፉ ሊወለወል ተሰጥቶአል፤ገዳዩ በእጁ እንዲጨብጠው፣ተስሎአል፤ ተወልውሎአል።

12. የሰው ልጅ ሆይ፤ ይህ በሕዝቤ ላይ፣በእስራኤልም መሳፍንት ሁሉ ላይ መጥቶአልና፤ጩኸት፣ ዋይታም አሰማ።እነርሱ ከሕዝቤ ጋር በአንድ ላይ፣ለሰይፍ ተጥለዋል፤ስለዚህ ደረትህን ምታ።

13. “ ‘ፈተና በእርግጥ ይመጣል፤ ሰይፉ የናቀው በትረ መንግሥት ዘላቂነት ባይኖረውስ? ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’

14. “እንግዲህ፣ የሰው ልጅ ሆይ፤ ትንቢት ተናገር፤በእጅህም አጨብጭብ፤ሰይፉ ሁለት ጊዜ፣ሦስት ጊዜም ይምታ፤በእጅጉ የሚገድል፣ለግድያ የሚሆን፣በየአቅጣጫውም የሚከባቸው ሰይፍ ነው።

15. ልብ ሁሉ ይቀልጥ ዘንድ፣የሚወድቁትም እንዲበዙ፣በበሮቻቸው ሁሉ፣የግድያውን ሰይፍ አኑሬአለሁ።ወዮ! እንዲያብረቀርቅ ተወልውሎአል፤ለመግደልም ተመዞአል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 21