ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 20:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. በዚያን ቀን፣ ከግብፅ አውጥቻቸው ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈስሰው፣ ወዳዘጋጀሁላቸውም ምድር እንደማስገባቸው ማልሁላቸው።’

7. እኔም፣ ‘እያንዳንዳችሁ ዐይኖቻችሁን ያሳረፋችሁባቸውን ርኩስ ምስሎች አስወግዱ፤ በግብፅ ጣዖታትም ራሳችሁን አታርክሱ፤ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ነኝ’ አልኋቸው።

8. “ ‘እነርሱ ግን በእኔ ላይ ዐመፁ፤ ሊሰሙኝም አልፈለጉም፤ ዐይኖቻቸውን ያሳረፉባቸውን ርኩስ ምስሎች አላስወገዱም፤ የግብፅንም ጣዖታት አልተዉም። እኔም በዚያው በግብፅ ምድር መዓቴን በላያቸው ላፈስ፣ ቍጣዬንም ላወርድባቸው ወስኜ ነበር።

9. ነገር ግን በመካከላቸው በኖሩባቸውና እስራኤልን ከግብፅ ምድር ለመታደግ ቃል ስገባ፣ በእነርሱ ዘንድ በተገለጥሁት በአሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ክብር ተቈጠብሁ።

10. ስለዚህ ከግብፅ አውጥቼ ወደ ምድረ በዳ አመጣኋቸው።

11. ሰው ቢጠብቀው ኖሮ በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን ሰጠኋቸው፤ ሕጌንም አስታወቅኋቸው።

12. ደግሞም እኔ እግዚአብሔር እንደ ቀደስኋቸው ያውቁ ዘንድ፣ በእኔና በእነርሱ መካከልም ምልክት እንዲሆን ሰንበቴን ሰጠኋቸው።

13. “ ‘ነገር ግን የእስራኤል ሕዝብ በምድረ በዳ ዐመፀብኝ፤ ሰው ቢጠብቀው በሕይወት የሚኖርበትን ሥርዐቴን አልጠበቁም፤ ሕጌንም ተላለፉ፤ ሰንበቴንም ፈጽሞ አረከሱ። እኔም መዓቴን ላፈስባቸው፣ በምድረ በዳም ላጠፋቸው ወስኜ ነበር።

14. ነገር ግን ከመካከላቸው ሳወጣቸው ባዩ አሕዛብ ፊት ስሜ እንዳይረክስ ስለ ስሜ ተቈጠብሁ።

15. ደግሞም ከምድር ሁሉ ይልቅ ውብ ወደሆነችው፣ ማርና ወተት ወደምታፈሰው፣ ወደ ሰጠኋቸውም ምድር እንደማላስገባቸው እጆቼን አንሥቼ በምድረ በዳ በፊታቸው ማልሁ፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 20