ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 18:22-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. በደሉ ሁሉ አይታሰብበትም፤ በጽድቅ መንገድ ሄዶአልና በሕይወት ይኖራል።

23. በውኑ ኀጢአተኛ ሲሞት ደስ ይለኛልን? ይላል ጌታ እግዚአብሔር። ይልቁን ከመንገዱ ተመልሶ በሕይወት ሲኖር ደስ አይለኝምን?

24. “ጻድቅ ሰው ግን ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ፣ ኀጢአተኛው የሚያደርገውንም አስጸያፊ ነገር ቢፈጽም፤ ይህ ሰው በውኑ በሕይወት ይኖራልን? ከሠራው ጽድቅ አንዱም አይታሰብለትም፤ ታማኝ ባለመሆኑና ከፈጸመው ኀጢአት የተነሣ ይሞታል።

25. “እናንተ ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ትላላችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስማ፤ መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነውስ የእናንተ መንገድ አይደለምን?

26. ጻድቅ ከጽድቁ ተመልሶ ኀጢአት ቢሠራ በኀጢአቱ ይሞታል፤ ከፈጸመውም በደል የተነሣ በሕይወት አይኖርም።

27. ኀጢአተኛው ግን ከክፉ ሥራው ተመልሶ በታማኝነትና በቅንነት ቢኖር ሕይወቱን ያድናል።

28. የፈጸመውን በደል ሁሉ ተገንዝቦ ካደረገው ክፋት ሁሉ ስለ ተመለሰ፣ ፈጽሞ በሕይወት ይኖራል እንጂ አይሞትም።

29. የእስራኤል ቤት ግን፣ ‘የጌታ መንገድ ቀና አይደለችም’ ይላል። የእስራኤል ቤት ሆይ! መንገዴ ቀና አይደለችምን? ቀና ያልሆነችውስ የእናንተ መንገድ አይደለችምን?

30. “የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ስለዚህ እንደየ ሥራችሁ በእያንዳንዳችሁ ላይ እፈርዳለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። እንግዲህ ንስሓ ግቡ በኀጢአት እንዳትጠፉ፣ ከኀጢአታችሁ ሁሉ ተመለሱ።

31. በእኔ ላይ የፈጸማችሁትን በደል ሁሉ ወደ ኋላ ጣሉት፤ አዲስ ልብና አዲስ መንፈስ ይኑራችሁ። የእስራኤል ቤት ሆይ፤ ለምን ትሞታላችሁ?

32. ማንም እንዲሞት አልሻምና፣ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ወደ እኔ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ!

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 18