ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 17:12-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “ለዚህ ዐመፀኛ ቤት እንዲህ በል፤ ‘የእነዚህ ነገሮች ትርጒም ምን እንደሆነ አታውቁምን?’ እንዲህ በላቸው፤ ‘የባቢሎን ንጉሥ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደ፤ ንጉሥዋንና መሳፍንቷን ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ይዞአቸው ተመለሰ።

13. ከንጉሣውያን ቤተ ሰብ አንዱን ወስዶ ከእርሱ ጋር ውል አደረገ፤ በመሐላም ቃል አስገባው፤ የምድሪቱንም ታላላቅ ሰዎች ማርኮ ወሰደ፤

14. ይኸውም የምድሪቱ መንግሥት ተዋርዳ የእርሱን ውል በመጠበቅ ብቻ እንድትኖር እንጂ፣ ዳግመኛ እንዳታንሰራራ ለማድረግ ነበር።

15. ንጉሡ ግን በእርሱ ላይ ዐመፀ፤ ፈረሶችና ብዙ ሰራዊት ለማግኘት መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ላከ፤ ይሳካለት ይሆን? እንዲህ ዐይነቱን ነገር የፈጸመ ያመልጣልን? ውል ያፈረሰስ ሳይቀጣ ይቀራልን?

16. “ ‘በሕያውነቴ እምላለሁ ይላል ልዑል እግዚአብሔር፤ መሐላውን ባቀለለበት፣ ውሉን ባፈረሰበት፣ በዙፋንም ላይ ባስቀመጠው ንጉሥ ምድር በባቢሎን ይሞታል።

17. በባቢሎናውያን ብዙ ሕይወት ለማጥፋት በከተማዋ ዙሪያ ዐፈር በሚደለድሉበትና ምሽግ በሚሠሩበት ጊዜ፣ ፈርዖን ከኀያል ሰራዊቱና ከብዙ ጭፍሮቹ ጋር በጦርነት ሊረዳው አይችልም።

18. ያደረገውን መሐላ በማቃለልና እጁን ያስገባበትን ውል በማፍረስ ይህን ሁሉ ስለ ፈጸመ ከቅጣት አያመልጥም።

19. “ ‘ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ በሕያውነቴ እምላለሁ ያቃለለውን መሐላዬንና ያፈረሰውን ኪዳኔን በራሱ ላይ አመጣለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 17