ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 16:47-63 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

47. አንቺም በእነርሱ መንገድ መሄድና አስጸያፊ ተግባራቸውን መከተል ብቻ ሳይሆን፣ ከእነርሱ ይልቅ ፈጥነሽ ምግባረ ብልሹ ሆንሽ።

48. እኔ ሕያው እግዚአብሔር! በራሴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴት ልጆችሽ ያደረጋችሁትን እኅትሽ ሰዶምና ልጆቿ እንኳ አላደረጉትም።

49. “ ‘እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር።

50. ኵራተኞች ነበሩ፤ በፊቴ አስጸያፊ ተግባር መፈጸማቸውን ባየሁ ጊዜም አስወገድኋቸው።

51. ሰማርያ አንቺ ያደረግሽውን ኀጢአት ግማሹን እንኳ አልሠራችም። አንቺ ግን ከእነርሱ የባሰ አስጸያፊ ተግባር በመፈጸምሽ፣ በዚህ ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው።

52. እኅቶችሽን እንደ ጻድቃን በማስቈ ጠርሽ፣ ዕፍረትሽን ተከናነቢ፤ ኀጢአትሽ ከኀጢአታቸው የከፋ ስለ ሆነ፣ እነርሱ ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ሆኑ። እንግዲህ እኅቶችሽን ጻድቃን ስላስመሰልሻቸው፣ አንቺ ተዋረጂ፤ ዕፍረትሽንም ተከናነቢ።

53. “ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ።

54. ይህም የሚሆነው ለእነርሱ መጽናኛ በመሆንሽ እንድ ትዋረጂና ባደረግሽው ሁሉ እንድታፍሪ ነው።

55. እኅቶችሽ ሰዶምና ሴት ልጆቿ እንዲሁም ሰማርያና ሴት ልጆቿ ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴት ልጆችሽም ቀድሞ ወደ ነበራችሁበት ሁኔታ ትመለሳላችሁ።

56. በታበይሽበት ወቅት የእኅትሽን የሰዶምን ስም ለመጥራት እንኳ ፈቃደኛ አልነበርሽም፤

57. ይህም ኀጢአትሽ ከመገለጡ በፊት ነበር። አሁን ግን በዙሪያሽ ሆነው ለሚንቁሽ ለኤዶም ሴት ልጆችና ለጐረቤቶቿ ሁሉ፣ እንዲሁም ለፍልስጥኤም ሴት ልጆች መሣለቂያ ሆነሻል።

58. ለብልግናሽና ለአስጸያፊ ተግባርሽ የሚገባውን ቅጣት ትሸከሚያለሽ፤ ይላል እግዚአብሔር።

59. “ ‘ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ቃል ኪዳኔን በማፍረስ መሐላዬን ንቀሻልና ተገቢውን ቅጣት ከእኔ ዘንድ ትቀበያለሽ።

60. ነገር ግን በልጅነትሽ ጊዜ ከአንቺ ጋር የገባሁትን ቃል ኪዳን አስባለሁ፤ ለዘላለምም የሚኖር ቃል ኪዳን ከአንቺ ጋር እመሠርታለሁ።

61. ከአንቺ ታላላቅ የሆኑትንና ታናናሽ የሆኑትን እኅቶችሽን ስትቀበዪ፣ አካሄድሽን ታስቢአለሽ፤ ታፍሪአለሽም። ሴት ልጆች እንዲሆኑሽም እነርሱን ለአንቺ እሰጣለሁ፤ ከአንቺ ጋር በገባሁት ቃል ኪዳን መሠረት ግን አይደለም።

62. ስለዚህ ከአንቺ ጋር ቃል ኪዳኔን ዐድሳለሁ፤ በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቂአለሽ።

63. ያደረግሽውን ሁሉ ይቅር ባልሁሽ ጊዜ፣ በደልሽ ትዝ ሲልሽ ታፍሪያለሽ፤ ከውርደትሽም የተነሣ አፍሽን ከቶ አትከፍቺም፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 16