ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 16:40-55 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

40. ሕዝብ ያነሣሡብሻል፤ በድንጋይ ይወግሩሻል፤ በሰይፍ ይቈራርጡሻል፤

41. ቤቶችሽን ያቃጥላሉ፤ በብዙ ሴቶችም ፊት ቅጣት ያመጡብሻል። ግልሙትናሽን አስተውሻለሁ፤ ከእንግዲህም ለወዳጆችሽ ዋጋ አትከፍዪም።

42. በዚህም በአንቺ ላይ የነበረው ቍጣዬ ይበርዳል፤ የቅናቴ ቍጣም ከአንቺ ይርቃል። እኔም ዝም እላለሁ፤ ከእንግዲህም አልቈጣም።

43. “ ‘በእነዚህ ነገሮች አስቈጣሽኝ እንጂ የልጅነትሽን ወራት አላሰብሽም፤ ስለዚህ የሥራሽን እከፍልሻለሁ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር። በሌላው አስጸያፊ ተግባርሽ ሁሉ ላይ ዘማዊነትን አልጨመርሽምን?

44. “ ‘በምሳሌ የሚናገር ሁሉ፣ “ሴት ልጅ በእናቷ ትወጣለች” እያለ ይመስልብሻል።

45. አንቺ ባሏንና ልጆቿን የምትጸየፍ የእናትሽ ልጅ ነሽ፤ ባሎቻቸውንና ልጆቻቸውን የሚጸየፉ የእኅቶችሽ እኅት ነሽ። እናታችሁ ኬጢያዊት፣ አባታችሁም አሞራዊ ነበሩ።

46. ታላቂቱ እኅትሽ ከአንቺ በስተ ሰሜን ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰማርያ ናት፤ ታናሺቱ እኅትሽም ከአንቺ በስተ ደቡብ ከሴት ልጆቿ ጋር የምትኖረው ሰዶም ናት።

47. አንቺም በእነርሱ መንገድ መሄድና አስጸያፊ ተግባራቸውን መከተል ብቻ ሳይሆን፣ ከእነርሱ ይልቅ ፈጥነሽ ምግባረ ብልሹ ሆንሽ።

48. እኔ ሕያው እግዚአብሔር! በራሴ እምላለሁ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ አንቺና ሴት ልጆችሽ ያደረጋችሁትን እኅትሽ ሰዶምና ልጆቿ እንኳ አላደረጉትም።

49. “ ‘እነሆ የእኅትሽ የሰዶም ኀጢአት ይህ ነበር፤ እርሷና ሴት ልጆቿ እብሪተኞች፣ ጥጋበኞችና ደንታ ቢሶች ነበሩ፤ ድኾችንና ችግረኞችንም አይረዱም ነበር።

50. ኵራተኞች ነበሩ፤ በፊቴ አስጸያፊ ተግባር መፈጸማቸውን ባየሁ ጊዜም አስወገድኋቸው።

51. ሰማርያ አንቺ ያደረግሽውን ኀጢአት ግማሹን እንኳ አልሠራችም። አንቺ ግን ከእነርሱ የባሰ አስጸያፊ ተግባር በመፈጸምሽ፣ በዚህ ሁሉ እኅቶችሽን ጻድቃን አስመሰልሻቸው።

52. እኅቶችሽን እንደ ጻድቃን በማስቈ ጠርሽ፣ ዕፍረትሽን ተከናነቢ፤ ኀጢአትሽ ከኀጢአታቸው የከፋ ስለ ሆነ፣ እነርሱ ከአንቺ ይልቅ ጻድቃን ሆኑ። እንግዲህ እኅቶችሽን ጻድቃን ስላስመሰልሻቸው፣ አንቺ ተዋረጂ፤ ዕፍረትሽንም ተከናነቢ።

53. “ ‘ነገር ግን የሰዶምንና የሴት ልጆቿን፣ እንዲሁም የሰማርያንና የሴት ልጆቿን ምርኮ እመልሳለሁ፤ የአንቺንም ምርኮ የእነርሱን በምመልስበት ጊዜ እመልሳለሁ።

54. ይህም የሚሆነው ለእነርሱ መጽናኛ በመሆንሽ እንድ ትዋረጂና ባደረግሽው ሁሉ እንድታፍሪ ነው።

55. እኅቶችሽ ሰዶምና ሴት ልጆቿ እንዲሁም ሰማርያና ሴት ልጆቿ ቀድሞ ወደነበሩበት ሁኔታ ይመለሳሉ፤ አንቺና ሴት ልጆችሽም ቀድሞ ወደ ነበራችሁበት ሁኔታ ትመለሳላችሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 16