ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 16:29-39 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

29. ርኵሰትሽንም እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ባቢሎን ድረስ አበዛሽ፤ ያም ሆኖ አልረካሽም።

30. “ ‘እንደ ዐይን አውጣ አመንዝራ ይህን ሁሉ መፈጸምሽ ምን ዐይነት ደካማ ልብ ቢኖርሽ ነው! ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

31. በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይ ጒብታሽን ባበጀሽና በየአደባባዩም መስገጃ ኰረብታ በሠራሽ ጊዜ እንደ ማንኛውም ዝሙት አዳሪ አልነበርሽም፤ ምክንያቱም ዋጋ አላስከፈልሽም።

32. “ ‘አንቺ ከገዛ ባሏ ይልቅ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ነሽ!

33. ማንኛዋም አመንዝራ ሴት ዋጋ ይከፈላታል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ስጦታ ታበረክቻለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ እጅ መንሻ ታቀርቢላቸዋለሽ።

34. ስለዚህ ያንቺ ግልሙትና ከሌሎቹ የተለየ ነው፤ ማመንዘር የሚሻ ማንም ሰው፣ አንቺን አሳዶ ማግባባት አያስፈልገውም። ዋጋ ትከፍያለሽ እንጂ አይከፈልሽም፤ አንቺ የሌሎች ፍጹም ተቃራኒ ነሽ።

35. “ ‘አንቺ አመንዝራ ሆይ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሚ!

36. ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ሀብትሽን ስላፈሰስሽ፣ ከወዳጆችሽ ጋር ያለ ገደብ ስላመነዘርሽና ዕርቃንሽን ስለ ገለጥሽ፣ ስለ አስጸያፊዎቹ ጣዖቶችሽ ሁሉና ለእነርሱም የልጆችሽን ደም ስላቀረብሽ፣

37. በዚህ ምክንያት ደስ የተሰኘሽባቸውን ወዳጆችሽን፣ የወደድሻቸውንና የጠላሻቸውን ሁሉ እሰበስባለሁ፤ ከየአቅጣጫው ሁሉ በዙሪያሽ እሰበስባቸዋለሁ፤ በፊታቸው ዕርቃንሽን እገልጣለሁ፤ እነርሱም ኀፍረተ ሥጋሽን ሁሉ ያያሉ።

38. ለአመንዝራና ለነፍሰ ገዳይ ሴቶች የሚገባውን ፍርድ እፈርድብሻለሁ፤ በመዓቴና በቅናቴ እስከ ደም እበቀልሻለሁ።

39. ለወዳጆችሽ አሳልፌ እሰጥሻለሁ፤ እነርሱም ጒብታሽንና የማምለኪያ ኰረብታሽን ያፈርሳሉ፤ ልብስሽን ይገፉሻል፤ ምርጥ ጌጣጌጥሽን ይቀሙሻል፤ ዕርቃንሽንና ባዶ እጅሽን ያስቀሩሻል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 16