ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 16:22-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. በእነዚህ አስጸያፊ ተግባሮችሽና አመንዝራነትሽ ሁሉ፣ ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የሕፃንነትሽ ወራት ትዝም አላለሽ!።

23. “ ‘ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከሌላው ክፋትሽ ሁሉ በተጨማሪ፣

24. ለራስሽ ጒብታን አበጀሽ፤ በየአደባባዩም የማምለኪያ ኰረብታ ሠራሽ።

25. በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይም የመስገጃ ኰረብታ አበጀሽ፤ ገላሽን ለዐላፊ አግዳሚው በማቅረብና አመንዝራነትሽን በማበራከት ውበትሽንም አረከስሽ።

26. ዘማውያን ከሆኑ ግብፃውያን ጎረቤቶችሽ ጋር አመነዘርሽ፤ ገደብ በሌለው የዝሙት ተግባርሽም ለቍጣ አነሣሣሽኝ።

27. ስለዚህ ክንዴን በአንቺ ላይ አንሥቼ ድርጎሽን ቀነስሁ፤ ከክፉ መንገድሽም የተነሣ በብልግናሽ ለሚያፍሩ ጠላቶችሽ ለፍልስጥኤማውያን ሴቶች ልጆች አሳልፌ ሰጠሁሽ።

28. ገና ስላልረካሽም ከአሦራውያን ጋር ደግሞ አመነዘርሽ፤ ከዚያም በኋላ እንኳ አልረካሽም።

29. ርኵሰትሽንም እስከ ነጋዴዎች ምድር እስከ ባቢሎን ድረስ አበዛሽ፤ ያም ሆኖ አልረካሽም።

30. “ ‘እንደ ዐይን አውጣ አመንዝራ ይህን ሁሉ መፈጸምሽ ምን ዐይነት ደካማ ልብ ቢኖርሽ ነው! ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

31. በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይ ጒብታሽን ባበጀሽና በየአደባባዩም መስገጃ ኰረብታ በሠራሽ ጊዜ እንደ ማንኛውም ዝሙት አዳሪ አልነበርሽም፤ ምክንያቱም ዋጋ አላስከፈልሽም።

32. “ ‘አንቺ ከገዛ ባሏ ይልቅ ሌሎችን የምታስተናግድ አመንዝራ ነሽ!

33. ማንኛዋም አመንዝራ ሴት ዋጋ ይከፈላታል፤ አንቺ ግን ለወዳጆችሽ ሁሉ ስጦታ ታበረክቻለሽ፤ ከየአቅጣጫው መጥተው ከአንቺ ጋር ያመነዝሩ ዘንድ እጅ መንሻ ታቀርቢላቸዋለሽ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 16