ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 16:10-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. ወርቀ ዘቦ አለበስሁሽ፤ ምርጥ ቈዳ ጫማም አደረግሁልሽ፤ ያማረ በፍታ አለበስሁሽ ውድ መደረቢያም አጐናጸፍሁሽ።

11. በጌጣጌጥ አንቈጠቈጥሁሽ፤ በእጅሽ አንባር፣ በዐንገትሽም ድሪ አጠለቅሁልሽ፤

12. በአፍንጫሽ ቀለበት፣ በጆሮሽ ጉትቻ፣ በራስሽም ላይ ውብ አክሊል አደረግሁልሽ፤

13. በወርቅና በብር አጌጥሽ፤ ልብስሽም ያማረ በፍታ፣ ሐርና ወርቀ ዘቦ ነበር፤ ምግብሽም የላመ ዱቄት፣ ማርና የወይራ ዘይት ነበር። እጅግ ውብ ሆንሽ፤ ንግሥት ለመሆንም በቃሽ።

14. እኔ ከሰጠሁሽ ሞገስ የተነሣ ውበትሽ ፍጹም በመሆኑ ዝናሽ በአሕዛብ መካከል ገነነ፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

15. “ ‘ነገር ግን በውበትሽ ተመካሽ፤ ዝናሽንም ለአመንዝራነት ተጠቀምሽበት፤ ከዐላፊ አግዳሚው ጋር ያለ ገደብ አመነዘርሽ ውበትሽም ለማንም ሆነ።

16. ከልብስሽ አንዳንዱን ወስደሽ የምታመነዝሪበትን መስገጃ ስፍራ አስጌጥሽበት፤ እንዲህ ዐይነት ነገር ከዚህ ቀደም አልታየም፤ ወደ ፊትም አይኖርም።

17. ከሰጠሁሽ ወርቄና ብሬ የተሠራውን ምርጥ ጌጣጌጥ ወስደሽ የወንድ ምስሎች ለራስሽ አበጀሽ፤ ከእነርሱም ጋር ዝሙት ፈጸምሽ።

18. ወርቀ ዘቦ ልብስሽን ወስደሽ ደረብሽላቸው፤ ዘይቴንና ዕጣኔንም በፊታቸው አቀረብሽ።

19. እንድትበዪ የሰጠሁሽን ምግብ ይኸውም ምርጡን ዱቄት፣ ማሩንና የወይራ ዘይቱን መልካም መዐዛ ያለው ዕጣን አድርገሽ አቀረብሽላቸው፤ እንዲህ ያለ ነገር ተፈጽሞአል፤ ይላል ጌታ እግዚአብሔር።

20. “ ‘ለእኔ የወለድሻቸውን ወንዶችና ሴቶች ልጆችሽን እንዲበሏቸው ለምስሎቹ ሠዋሽላቸው፤ አመንዝራነትሽ አንሶ ነውን?

21. ልጆቼን ዐርደሽ ለጣዖት መሥዋዕት አድርገሽ አቀረብሻቸው።

22. በእነዚህ አስጸያፊ ተግባሮችሽና አመንዝራነትሽ ሁሉ፣ ከእናትሽ ማሕፀን እንደ ወጣሽ ዕርቃንሽን ሆነሽ በደምሽ ውስጥ ስትንፈራገጪ የነበርሽበት የሕፃንነትሽ ወራት ትዝም አላለሽ!።

23. “ ‘ወዮ! ወዮልሽ! ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ከሌላው ክፋትሽ ሁሉ በተጨማሪ፣

24. ለራስሽ ጒብታን አበጀሽ፤ በየአደባባዩም የማምለኪያ ኰረብታ ሠራሽ።

25. በየመንገዱ መጠምዘዣ ላይም የመስገጃ ኰረብታ አበጀሽ፤ ገላሽን ለዐላፊ አግዳሚው በማቅረብና አመንዝራነትሽን በማበራከት ውበትሽንም አረከስሽ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 16