ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሕዝቅኤል 12:12-20 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. “በመካከላቸው ያለው መስፍን በምሽት ጓዙን በትከሻው ተሸክሞ ይወጣል፤ ሾልኮ እንዲሄድ ግንቡ ይነደልለታል፤ ምድሪቱንም እንዳያይ ፊቱን ይሸፍናል።

13. መረቤን በእርሱ ላይ እዘረጋለሁ፤ በወጥመዴም ይያዛል፤ ወደ ከለዳውያን ምድር ወደ ባቢሎን አመጣዋለሁ፤ ነገር ግን እርሷን ሳያያት በዚያ ይሞታል።

14. በዙሪያው ያሉትን ረዳቶቹንና ወታደሮቹን ሁሉ ወደ ነፋስ እበትናቸዋለሁ፤ በተመዘዘም ሰይፍ አሳድዳቸዋለሁ።

15. “በአሕዛብ መካከል ስበትናቸውና በአገሮችም መካከል ስዘራቸው፤ በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።

16. ነገር ግን በሄዱባቸው አሕዛብ መካከል ስለ ጸያፍ ተግባራቸው ይናገሩ ዘንድ ከእነርሱ ጥቂቶቹን ከሰይፍ ከራብና ከቸነፈር አተርፋለሁ። በዚያን ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ያውቃሉ።”

17. የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ እኔ መጣ፤

18. “የሰው ልጅ ሆይ፤ ምግብህን በድንጋጤ ብላ፤ ውሃህንም በፍርሀትና በመንቀጥቀጥ ጠጣ።

19. ለምድሪቱ ሕዝብ እንዲህ በል፤ ‘ጌታ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌምና በእስራኤል ምድር ስለሚኖሩት እንዲህ ይላል፤ “በዚያ ከሚኖሩ ሰዎች ሁሉ ዐመፅ የተነሣ ምድራቸው ስለምትራቈት፣ ምግባቸውን በጭንቀት ይመገባሉ፤ ውሃቸውንም በፍርሀት ይጠጣሉ።

20. ሰው ይኖርባቸው የነበሩ ከተሞች ባድማ ይሆናሉ፤ ምድሪቱም ወና ትሆናለች። በዚያ ጊዜ እኔ እግዚአብሔር እንደሆንሁ ታውቃላችሁ።’ ”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሕዝቅኤል 12