ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሐጌ 2:12-23 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. አንድ ሰው የተቀደሰውን ሥጋ በልብሱ ዕጥፋት ቢይዝ፣ ያም ዕጥፋት እንጀራ ወይም ወጥ፣ የወይን ጠጅ ወይም ዘይት ወይም ሌላ ምግብ ቢነካ የተቀደሰ ይሆናልን?”ካህናቱም፣ “የተቀደሰ አይሆንም” ብለው መለሱ።

13. ሐጌም፣ “ሬሳ በመንካቱ የረከሰ ሰው፣ ከእነዚህ አንዱን ቢነካ፣ የተነካው ነገር ይረክሳልን?” ሲል ጠየቀ።ካህናቱም፣ “አዎን፣ ይረክሳል” ሲሉ መለሱ።

14. ከዚያም ሐጌ እንዲህ አለ፤ “ ‘ይህ ሕዝብና ይህ ወገንም በፊቴ እንደዚሁ ነው’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘የእጃቸው ሥራና የሚያቀርቡት ሁሉ የረከሰ ነው’።

15. “ ‘እንግዲህ ከዛሬ ጀምራችሁ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ድንጋይ በድንጋይ ላይ ከመነባበሩ በፊት የነበረውን ሁኔታ አስተውሉ።

16. አንድ ሰው ሃያ መስፈሪያ ወደ ሚሆን የእህል ክምር በመጣ ጊዜ ዐሥር ብቻ አገኘ፤ አምሳ ማድጋ የወይን ጠጅ ለመቅዳት ወደ መጭመቂያው በሄደ ጊዜ ሃያ ብቻ አገኘ፤

17. የእጃችሁን ሥራ ሁሉ በዋግ፣ በአረማሞና በበረዶ መታሁት፤ እናንተ ግን ወደ እኔ አልተመለሳችሁም’ ይላል እግዚአብሔር፤

18. ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ፣ ይኸውም ከዘጠነኛው ወር ሃያ አራተኛ ቀን ጀምሮ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መሠረት እስከ ተጣለበት ቀን ድረስ ያለውን ዘመን አስተውሉ፤ ልብ ብላችሁም አስቡ፤

19. በጐተራ የቀረ ዘር አሁንም ይገኛልን? የወይኑና የበለሱ ዛፍ፣ የሮማኑና የወይራው ዛፍ እስካሁን አላፈሩም።“ ‘ከዚህ ቀን ጀምሮ እባርካችኋለሁ።’ ”

20. በወሩ ሃያ አራተኛ ቀን የእግዚአብሔር ቃል ዳግመኛ እንዲህ ሲል ወደ ሐጌ መጣ፤

21. “ለይሁዳ ገዥ ለዘሩባቤል ሰማያትንና ምድርን እንደማናውጥ ንገረው፤

22. የመንግሥታትን ዙፋን እገለብጣለሁ፤ የባዕዳንን መንግሥታት ኀይል አጠፋለሁ፤ ሠረገሎችንና ሠረገለኞችን እገለብጣለሁ፤ ፈረሶችና ጋላቢዎቻቸውም በገዛ ወንድሞቻቸው ሰይፍ ይወድቃሉ።

23. “ ‘እግዚአብሔር ጸባኦት እንዲህ ይላል፤ ‘በዚያን ቀን ባሪያዬ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል ሆይ፤ እኔ እወስድሃለሁ’ ይላል እግዚአብሔር፤ ‘እንደ ማተሚያ ቀለበቴ አደርግሃለሁ፤ እኔ መርጬአለሁና’ ይላል እግዚአብሔር ጸባኦት።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሐጌ 2