ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሆሴዕ 2:1-16 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. “ወንድሞቻችሁን ‘ሕዝቤ’፣ እኅቶቻችሁንም ‘ተወዳጆቼ’ ብላችሁ ጥሯቸው።

2. “እናታችሁን ምከሯት፤ ምከሯት፤እርሷ ሚስቴ አይደለችም፤እኔም ባሏ አይደለሁምና።ከፊቷ የዘማዊነት አስተያየትን፣ከጡቶቿም መካከል ምንዝርናዋን ታስወግድ።

3. አለበለዚያ ገፍፌ ዕርቃኗን አስቀራታለሁ፤እንደ ተወለደችበትም ቀን አደርጋታለሁ፤እንደ ምድረ በዳ፣እንደ ደረቅም ምድር አደርጋታለሁ፤በውሃ ጥምም እገድላታለሁ።

4. ለልጆቿ አልራራላቸውም፤የምንዝርና ልጆች ናቸውና።

5. እናታቸው አመንዝራ ነች፤በውርደትም ፀንሳቸዋለች፤እርሷም፣ ‘እንጀራዬንና ውሃዬን ይሰጡኛል፤ሱፌንና የሐር ልብሴን፣ ዘይቴንና መጠጤን ይሰጡኛል፤ስለዚህ ውሽሞቼን ተከትዬ እሄዳለሁ’ አለች።

6. በዚህ ምክንያት መንገዷን በእሾህ እዘጋለሁ፤መውጫ መንገድ እንዳታገኝም ዙሪያዋን በግንብ አጥራለሁ።

7. ውሽሞቿን ተከትላ ትሄዳለች፤ ነገር ግን አትደርስባቸውም፤ትፈልጋቸዋለች፤ ሆኖም አታገኛቸውም።ከዚያም እንዲህ ትላለች፤‘ወደ ቀድሞ ባሌ እመለሳለሁ፤የፊተኛው ኑሮዬ ከአሁኑ ይሻለኛልና።’

8. እርሷም እህል፣ ዘይትና አዲስ የወይን ጠጅ የሰጠኋት፣ለበኣል አምልኮ ያደረጉትን፣ብርንና ወርቅን ያበዛሁላት፣እኔ እንደሆንሁ አላወቀችም።

9. “ስለዚህ እህሌን በመከር ጊዜ፣አዲሱም የወይን ጠጅ በደረሰ ጊዜ እወስዳለሁ፤ዕርቃኗንም እንዳትሸፍንበት፣ሱፍና የሐር ልብሴን መልሼ እወስድባታለሁ።

10. አሁንም በውሽሞቿ ፊት፣ነውሯን እገልጣለሁ፤ከእጄም የሚያድናት የለም።

11. የደስታ በዓሎቿን ሁሉ፣የዓመት በዓሎቿንና፣ የወር መባቻዎቿንሰንበቶቿንና የተመረጡ በዓሎቿን ሁሉ አስቀራለሁ።

12. ከውሽሞቼ የተቀበልሁት ዋጋ ነው የምትለውን፤የወይን ተክሎቿንና የበለስ ዛፎቿን አጠፋለሁ፤ጫካ አደርገዋለሁ፤የዱር አራዊትም ይበሉታል።

13. ለበኣል አማልክት፣ ዕጣን ስላጠነችባቸው ቀናትእቀጣታለሁ፤በጌጣ ጌጥና በቀለበቶች ራሷን አስጊጣለች፤ውሽሞቿንም ተከትላ ሄዳለች፤እኔን ግን ረስታለች”ይላል እግዚአብሔር።

14. “ስለዚህ እነሆ፤ አባብላታለሁ፤ወደ ምድረ በዳም እወስዳታለሁ፤በፍቅር ቃል አነጋግራታለሁ።

15. በዚያም የወይን ተክሏን እመልስላታለሁ፤የአኮርንም ሸለቆ የተስፋ በር እንዲሆናት አደርጋለሁ።በዚያም ከግብፅ እንደ ወጣችበት ቀን፣እንደ ልጅነቷም ጊዜ ትዘምራለች።

16. “በዚያ ቀን፣ ‘ባሌ’ ብለሽ፣ትጠሪኛለሽ” ይላል እግዚአብሔር።“ከእንግዲህም፣ ‘ጌታዬ’ ብለሽ አትጠሪኝም።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሆሴዕ 2