ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

ሆሴዕ 14:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እስራኤል ሆይ፤ በኀጢአትህ ምክንያት ስለ ወደቅህ፣ወደ አምላክህ ወደ እግዚአብሔር ተመለስ።

2. የምትሉትን ቃል ይዛችሁ፣ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ፤እንዲህም በሉት፤“ኀጢአታችንን ሁሉ ይቅር በለን፤የከንፈራችንንም ፍሬ እንድናቀርብ፣በምሕረትህ ተቀበለን።

3. አሦር ሊያድነን አይችልም፤በጦር ፈረሶችም ላይ አንቀመጥም፤ከእንግዲህም የገዛ እጆቻችን የሠሯቸውን፣‘አምላኮቻችን’ አንላቸውም፤ድኻ አደጉ ከአንተ ርኅራኄ ያገኛልና።”

4. “እኔ ከዳተኛነታቸውን እፈውሳለሁ፤እንዲሁ እወዳቸዋለሁ፤ቊጣዬ ከእነርሱ ተመልሶአልና።

5. እኔ ለእስራኤል እንደ ጠል እሆናለሁ፤እንደ ውብ አበባ ያብባል፤እንደ ሊባኖስ ዝግባም፣ሥር ይሰዳል፤

6. ቅርንጫፉ ያድጋል፤ውበቱ እንደ ወይራ ዛፍ፣ሽታውም እንደ ሊባኖስ ዝግባ ይሆናል።

7. ሰዎች እንደ ገና ከጥላው በታች ያርፋሉ፤እርሱም እንደ እህል ይለመልማል፤እንደ ወይን ተክል ያብባል፤ዝናውም እንደ ሊባኖስ የወይን ጠጅ ይወጣል።

8. ኤፍሬም ሆይ፤ ከእንግዲህ ከጣዖት ጋርምን ጒዳይ አለኝ?የምሰማህና የምጠነቀቅልህ እኔ ነኝ፤እኔ እንደለመለመ የጥድ ዛፍ ነኝ፤ፍሬያማነትህም ከእኔ የተነሣ ነው።”

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ ሆሴዕ 14