ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 6:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚያም ሰሎሞን እንዲህ አለ፤ “እግዚአብሔር ጥቅጥቅ ባለ ደመና ውስጥ እንደሚኖር ተናግሮአል፤

2. እኔም አንተ ለዘላለም ትኖርበት ዘንድ፣ ይህን ታላቅና ድንቅ ቤተ መቅደስ ሠራሁልህ።”

3. መላው የእስራኤል ጉባኤ እዚያው ቆመው ሳሉ፣ ንጉሡ ዘወር ብሎ ባረካቸው፤

4. እንዲህም አለ፤“ለአባቴ ለዳዊት በቃሉ የሰጠውን ተስፋ በእጁ የፈጸመ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ይመስገን፤ እንዲህ ብሏልና፤

5. ‘ሕዝቤን ከግብፅ ካወጣሁበት ጊዜ ጀምሮ፣ ስሜ የሚጠራበት ቤተ መቅደስ ይሠራበት ዘንድ ከማናቸውም የእስራኤል ነገድ ከተሞች አንድም አልመረጥሁም፤ ወይም የሕዝቤ የእስራኤል መሪ ይሆን ዘንድ ማንንም አልመረጥሁም።

6. አሁን ግን ስሜ በዚያ እንዲሆን ኢየሩሳሌምን፣ ሕዝቤን እስራኤልን እንዲገዛም ዳዊትን መርጫለሁ።”

7. “አባቴ ዳዊት፣ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔር ስም ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልቡ አስቦ ነበር፤

8. እግዚአብሔር ግን፣ ለአባቴ ለዳዊት እንዲህ አለው፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ ለመሥራት በልብህ አስበህ ነበር፤ ይህን በልብህ በማሰብህ መልካም አድርገሃል፤

9. ይሁን እንጂ ቤተ መቅደሱን የምትሠራው አንተ አይደለህም፤ ለስሜ ቤተ መቅደስ የሚሠራልኝ ከአብራክህ የሚከፈለው፣ የገዛ ልጅህ ነው።’

10. “እግዚአብሔርም የተናገረውን ቃል ፈጽሞአል፤ እኔም እግዚአብሔር በሰጠው ተስፋ መሠረት በአባቴ በዳዊት እግር ተተክቼ፣ በእስራኤል ዙፋን ላይ ተቀምጫለሁ፤ ለእስራኤል አምላክ ለእግዚአብሔርም ስም ቤተ መቅደስ ሠርቻለሁ።

11. በዚያም እግዚአብሔር ከእስራኤል ሕዝብ ጋር ያደረገው ኪዳን ያለበትን ታቦት አኑሬአለሁ።”

12. ከዚህ በኋላ ሰሎሞን መላው የእስራኤል ጉባኤ ባሉበት በእግዚአብሔር መሠዊያ ፊት እጆቹን ዘርግቶ ቆመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 6