ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 35:8-25 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ።

9. ደግሞም ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያና ናትናኤል እንደዚሁም የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸቢያ፣ ይዔኤልና ዮዛባት ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ አምስት ሺህ በግና ፍየል አምስት መቶም በሬ ለሌዋውያኑ ሰጧቸው።

10. የአገልግሎቱ ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ፣ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየክፍላቸው ከተመደቡት ሌዋውያን ጋር ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ።

11. የፋሲካው በጎች ታረዱ፤ ካህናቱ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የበጎቹን ቈዳ ገፈፉ።

12. በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡም፣ እንደየቤተ ሰቡና እንደየምድቡ ለሕዝቡ ለመስጠት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ፤ ወይፈኖቹንም እንደዚሁ አደረጉ።

13. እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ።

14. ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ።

15. መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለ ራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።

16. በዚህ ዓይነት የፋሲካን በዓል በማክበርና የሚቃጠል መሥዋዕት በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ በማቅረብ የእግዚአብሔር አግልግሎት ሁሉ ንጉሥ ኢዮስያስ ባዘዘው መሠረት በዚያኑ ቀን ተከናወነ።

17. በዚያን ጊዜ በስፍራው የተገኙ እስራኤላውያን የፋሲካን በዓል አከበሩ፤ የቂጣንም በዓል እንደዚሁ ሰባት ቀን አከበሩ።

18. ከነቢዩ ከሳሙኤል ዘመን ወዲህ እንዲህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ተከብሮ አያውቅም፤ ኢዮስያስ ከካህናቱ፣ ከሌዋውያኑ፣ ከመላው ይሁዳና ከእስራኤል፣ በዚያ ከነበሩትም ከኢየሩሳሌም ሰዎች ጋር እንዳከበረው አድርጎ ያከበረ አንድም የእስራኤል ንጉሥ የለም።

19. ይህ ፋሲካ የተከበረው በኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት በዐሥራ ስምንኛው ዓመት ነበር።

20. ከዚህ ሁሉ በኋላ ኢዮስያስ ቤተ መቅደሱን አደራጅቶ ባጠናቀቀ ጊዜ፣ የግብፅ ንጉሥ ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ፣ በከርከሚሽ ላይ ለመዋጋት ወጣ፤ ኢዮስያስም ጦርነት ሊገጥመው ወጣ።

21. ኒካዑ ግን፣ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፤ አንተንና እኔን የሚያጣላን ምንድ ነው? ጦርነት ከገጠምሁት ቤት ጋር እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንተን የምወጋህ አይደለሁም፤ እግዚአብሔር እንድፈጥን አዞኛል፤ ስለዚህ ከእኔ ጋር ያለውን እግዚአብሔርን መቃወምህን ተው፤ ያለዚያ ያጠፋሃል” አለው።

22. ኢዮስያስ ግን ሌላ ሰው መስሎ በጦርነት ሊገጥመው ወጣ እንጂ ወደ ኋላ አልተመለሰም፤ በመጊዶ ሜዳ ላይ ሊዋጋው ሄደ እንጂ ኒካዑ ከእግዚአብሔር ታዞ የነገረውን ሊሰማ አልፈለገም።

23. ቀስተኞች ንጉሥ ኢዮስያስን ወጉት፤ እርሱም የጦር መኮንኖቹን፣ “ክፉኛ ቈስያለሁና ከዚህ አውጡኝ” አላቸው።

24. ስለዚህ ከሠረገላው አውርደው በራሱ ሠረገላ ላይ አስቀምጠውት ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ እዚያም ሞተ፤ በአባቶቹ መካነ መቃብር ተቀበረ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሁሉ አለቀሱለት።

25. ኤርምያስ ለኢዮስያስ የሐዘን እንጒርጒሮ ግጥም ጻፈለት፤ ወንዶችና ሴቶች ሙሾ አውራጆች ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ በዚህ ግጥም ኢዮስያስን ያስታውሱታል፤ ይህም በእስራኤል የተለመደ ሆኖ በልቅሶ ግጥም መጽሐፍ ተጽፎአል።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 35