ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 35:7-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

7. ኢዮስያስም እዚያ ለነበሩት ሕዝብ ሁሉ ለፋሲካው መሥዋዕት እንዲሆኑ ባጠቃላይ ሠላሳ ሺህ በግና ፍየል እንዲሁም ሦስት ሺህ ወይፈን ከራሱ ሀብት ሰጠ።

8. ሹማምቱም ለሕዝቡ፣ ለካህናቱና ለሌዋውያኑ በገዛ ፈቃዳቸው አዋጥተው ሰጡ። የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አለቆች የሆኑት ኬልቅያስ፣ ዘካርያስና ይሒኤልም ለፋሲካ መሥዋዕት የሚቀርቡ ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በግ እንዲሁም ሦስት መቶ ወይፈን ሰጡ።

9. ደግሞም ኮናንያ፣ ወንድሞቹ ሸማያና ናትናኤል እንደዚሁም የሌዋውያኑ መሪዎች ሐሸቢያ፣ ይዔኤልና ዮዛባት ለፋሲካ መሥዋዕት እንዲሆኑ አምስት ሺህ በግና ፍየል አምስት መቶም በሬ ለሌዋውያኑ ሰጧቸው።

10. የአገልግሎቱ ዝግጅት በተጠናቀቀ ጊዜ፣ ንጉሡ ባዘዘው መሠረት ካህናቱ በየክፍላቸው ከተመደቡት ሌዋውያን ጋር ቦታ ቦታቸውን ይዘው ቆሙ።

11. የፋሲካው በጎች ታረዱ፤ ካህናቱ የተቀበሉትን ደም ረጩ፤ ሌዋውያኑም የበጎቹን ቈዳ ገፈፉ።

12. በሙሴ ሕግ እንደ ተጻፈው ለእግዚአብሔር እንዲያቀርቡም፣ እንደየቤተ ሰቡና እንደየምድቡ ለሕዝቡ ለመስጠት የሚቃጠለውን መሥዋዕት ለዩ፤ ወይፈኖቹንም እንደዚሁ አደረጉ።

13. እነርሱም የፋሲካውን መሥዋዕት በሥርዐቱ መሠረት ጠበሱ፤ የተቀደሰውንም ቍርባን በምንቸት፣ በሰታቴና በድስት ቀቀሉ፤ ወዲያውኑም ለሕዝቡ አደሉ።

14. ከዚህ በኋላ ለራሳቸውና ለካህናቱ ዝግጅት አደረጉ፤ ምክንያቱም ካህናቱ የአሮን ልጆች የሚቃጠለውን መሥዋዕትና ስቡን እስከ ሌሊት ድረስ ያቀርቡ ስለ ነበር ነው። ስለዚህ ሌዋውያኑ ለራሳቸውና ለካህናቱ ለአሮን ልጆች ዝግጅት አደረጉ።

15. መዘምራኑ የአሳፍ ዘሮች በዳዊት፣ በአሳፍ፣ በኤማንና በንጉሡ ባለ ራእይ በኤዶታም በተሰጠው መመሪያ መሠረት በቦታቸው ነበሩ። በእያንዳንዱ በር ላይ የነበሩት በር ጠባቂዎችም ሌዋውያን ወገኖቻቸው ስላዘጋጁላቸው፣ ከጥበቃ ቦታቸው መለየት አያስፈልጋቸውም ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 35