ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 34:8-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

8. ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት፣ ምድሪቱንና ቤተ መቅደሱን ካነጻ በኋላ፣ የኤዜልያስን ልጅ ሳፋንን፣ የከተማዪቱን ገዥ መዕሤያንና የጸሓፊውን የኢዮአካዝን ልጅ ኢዮአክን የአምላኩን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይጠግኑ ዘንድ ላካቸው።

9. እነርሱም ወደ ሊቀ ካህኑ ወደ ኬልቅያስ ሄደው፣ ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የመጣውን ገንዘብ ሰጡት፤ ገንዘቡም በር ጠባቂዎች የነበሩት ሌዋውያን፣ ከምናሴ፣ ከኤፍሬምና ከመላው የእስራኤል ቅሬታዎች እንደዚሁም ከመላው ይሁዳና ከብንያም፣ ከኢየሩሳሌምም ነዋሪዎች የሰበሰቡት ነበር።

10. እነርሱም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሥራ እየተቈጣጠሩ እንዲያሠሩ ለተሾሙት ሰዎች ዐደራ ሰጡ፤ እነዚህም ሰዎች ገንዘቡን ቤተ መቅደሱን ለጠገኑትና ላደሱት ሰዎች ከፈሉ።

11. እንዲሁም የይሁዳ ነገሥታት እንዲፈርሱ ላደረጓቸው ሕንጻዎች ጥርብ ድንጋዮችን፣ ሠረገላዎችንና ማገጣጠሚያ ዕንጨቶችን እንዲገዙ ለዐናጢዎችና ለግንበኞች ገንዘብ ሰጡ።

12. ሰዎቹም ሥራውን በታማኝነት አከናወኑ። የበላይ ሆነው አመራር የሚሰጧቸውም ከሜራሪ ጐሣ የሆኑት ሌዋውያን፣ ኢኤትና አብድዩ፣ ከቀዓት ጐሣ ዘካርያስና ሜሱላም ነበሩ። በዜማ ዕቃ የላቀ ችሎታ የነበራቸው ሌዋውያን ሁሉ፣

13. የጒልበት ሠራተኞች ኀላፊ በመሆን፣ በየሥራው ላይ የተመደቡትን ሠራተኞች ይቈጣጠሩ ነበር። ጥቂቶቹ ሌዋውያን ደግሞ ኀላፊዎች፣ ጸሓፊዎችና በር ጠባቂዎች ነበሩ።

14. ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የገባውን ገንዘብ በሚያወጡበት ጊዜ፣ ካህኑ ኬልቅያስ በሙሴ አማካይነት የተሰጠውን የእግዚአብሔርን ሕግ መጽሐፍ አገኘ።

15. ኬልቅያስም ጸሓፊውን ሳፋንን፣ “የሕጉን መጽሐፍ በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ውስጥ አገኘሁት” አለው፤ ከዚያም መጽሐፉን ለሳፋን ሰጠው።

16. ሳፋንም መጽሐፉን ወደ ንጉሡ ወስዶ እንዲህ አለው፤ “ሹማምትህ የታዘዙትን ሁሉ በመፈጸም ላይ ናቸው፤

17. በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የነበረውንም ገንዘብ አውጥተው ለተቈጣጣሪዎቹና ለሠራተኞቹ አስረክበዋል።”

18. ከዚያም ጸሓፊው ሳፋን ንጉሡን፣ “ካህኑ ኬልቅያስ መጽሐፍ ሰጥቶኛል” አለው። ሳፋንም መጽሐፉን ለንጉሡ አነበበለት።

19. ንጉሡም የሕጉን ቃል በሰማ ጊዜ ልብሱን ቀደደ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 34