ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 30:6-15 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. መልእክተኞችም በንጉሡ ትእዛዝ፣ የንጉሡንና የሹማምቱን ደብዳቤ ይዘው ወደ እስራኤልና ወደ ይሁዳ ሁሉ ሄዱ፤ ደብዳቤውም እንዲህ የሚል ነበር፤“የእስራኤል ሕዝብ ሆይ፤ እርሱ ወደ ተረፋችሁት፣ ከአሦር ነገሥታትም እጅ ወዳመለጣችሁት፣ ወደ እናንተ እንዲመለስ እናንተም የአብርሃም፣ የይስሐቅና የእስራኤል አምላክ ወደ ሆነው ወደ እግዚአብሔር ተመለሱ።

7. እንደምታዩት ሁሉ መሣለቂያ እስኪያደርጋቸው ድረስ፣ ለአባቶቻቸው አምላክ ለእግዚአብሔር እንዳልታመኑ እንደ አባቶቻችሁና እንደ ወንድሞቻችሁ አትሁኑ።

8. እንደ አባቶቻችሁም አንገተ ደንዳኖች አትሁኑ፤ ለእግዚአብሔር ተገዙ፤ እርሱ ለዘላለም ወደ ቀደሰውም መቅደስ ኑ። አስፈሪ ቊጣው ከእናንተ እንዲመለስም፣ እግዚአብሔር አምላካችሁን አገልግሉ።

9. እናንተ ወደ እግዚአብሔር ብትመለሱ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና ርኅሩኅ ስለ ሆነ ወንድሞቻችሁና ልጆቻችሁን በማረኳቸው ዘንድ ምሕረትን ያገኛሉ፤ ወደዚህች ምድር ይመለሳሉ። እናንተ ወደ እርሱ ብትመለሱ፣ እርሱም ፊቱን ከእናንተ አይመልስም።

10. መልእክተኞቹም በኤፍሬምና በምናሴ ምድር ካንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመዘዋወር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ ሕዝቡ ግን አንቋሸሻቸው፤ ተሣለቀባቸውም።

11. ሆኖም ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

12. እንዲሁም ንጉሡና ሹማምቱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ያዘዙትን እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ነበር።

13. በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ።

14. በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎች ነቃቅለው፣ የዕጣን መሠዊያዎችንም ከስፍራው አንሥተው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣሉ።

15. በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ስለ ነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመጡ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 30