ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 30:10-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

10. መልእክተኞቹም በኤፍሬምና በምናሴ ምድር ካንዱ ከተማ ወደ ሌላው ከተማ በመዘዋወር እስከ ዛብሎን ድረስ ሄዱ፤ ሕዝቡ ግን አንቋሸሻቸው፤ ተሣለቀባቸውም።

11. ሆኖም ከአሴር፣ ከምናሴና ከዛብሎን ጥቂት ሰዎች ራሳቸውን ዝቅ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም መጡ።

12. እንዲሁም ንጉሡና ሹማምቱ በእግዚአብሔር ቃል መሠረት ያዘዙትን እንዲፈጽሙ አንድ ልብ ይሰጣቸው ዘንድ የእግዚአብሔር እጅ በይሁዳ ላይ ነበር።

13. በሁለተኛው ወር የቂጣን በዓል ለማክበር እጅግ ብዙ ሕዝብ በኢየሩሳሌም ተሰበሰበ።

14. በኢየሩሳሌም የነበሩትን መሠዊያዎች ነቃቅለው፣ የዕጣን መሠዊያዎችንም ከስፍራው አንሥተው ወደ ቄድሮን ሸለቆ ጣሉ።

15. በሁለተኛው ወር በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ዐረዱ። ካህናቱና ሌዋውያኑ አፍረው ስለ ነበር ራሳቸውን ቀደሱ፤ የሚቃጠል መሥዋዕትንም ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመጡ።

16. ከዚያም በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ ሕግ እንደታዘዘው መደበኛ ቦታቸውን ያዙ። ካህናቱም ከሌዋውያኑ እጅ የተቀበሉትን ደም ረጩ።

17. ከጉባኤው መካከል አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያልቀደሱ ስለ ነበሩ፣ ሌዋውያኑ በሥርዐቱ መሠረት ራሳቸውን ላላነጹትና ጠቦቶቻቸውን ለእግዚአብሔር መቀደስ ላልቻሉት ሁሉ የፋሲካውን በጎች ማረድ ነበረባቸው።

18. ምንም እንኳ ከኤፍሬም፣ ከምናሴ፣ ከይሳኮርና ከዛብሎን ከመጡት አብዛኛዎቹ ራሳቸውን ያላነጹ ቢሆንም ከተጻፈው ትእዛዝ ውጭ ፋሲካውን በሉ። ሕዝቅያስ ግን እንዲህ ሲል ጸለየ፤ “ቸሩ እግዚአብሔር ሆይ፤ ይቅር በላቸው፤

19. ምንም እንኳ በመቅደሱ ሥርዐት መሠረት የነጹ ሆነው ባይገኙም የአባቶቻቸው አምላክ የሆነውን እግዚአብሔር አምላካቸውን ለመፈለግ ልባቸውን የሚያዘጋጁትን ሁሉ ይቅር በላቸው።”

20. እግዚአብሔርም ሕዝቅያስን ሰማው፤ ሕዝቡንም ፈወሰ።

21. ሌዋውያኑና ካህናቱ በእግዚአብሔር የዜማ ዕቃ ታጅበው፣ በየዕለቱ ለእግዚአብሔር እየዘመሩ፣ በኢየሩሳሌም የነበሩት እስራኤላውያን የቂጣን በዓል በታላቅ ደስታ ለሰባት ቀን አከበሩ፤

22. ሕዝቅያስም በእግዚአብሔር አገልግሎት አስተዋዮች የነበሩትን ሌዋውያን ሁሉ በንግግሩ አበረታታ። ሰባቱንም ቀን የተወሰነላቸውን ድርሻ እየበሉና የኅብረት መሥዋዕቱንም እያቀረቡ የአባቶቻቸውን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

23. ጉባዔውም ሁሉ በተከታዩ ሰባት ቀን በዓሉን እንደ ገና ለማክበር ተስማሙ፣ ስለዚህ በዓሉን ለሰባት ተጨማሪ ቀን በታላቅ ደስታ አከበሩ።

24. የይሁዳ ንጉሥ ሕዝቅያስ አንድ ሺህ ወይፈን፣ ሰባት ሺህ በግና ፍየል ለጉባኤው ሰጠ፤ ሹማምቱም እንደዚሁ አንድ ሺህ ወይፈን፣ ዐሥር ሺህ በግና ፍየል ሰጡ። እጅግ ብዙ ካህናትም ራሳቸውን ቀደሱ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 30