ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 28:11-24 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

11. እንግዲህ ስሙኝ፤ የእግዚአብሔር አስፈሪ ቊጣ በእናንተ ላይ ነዶአልና፣ በምርኮ ያመጣችኋቸውን ወገኖቻችሁን መልሷቸው።”

12. ከዚያም ከኤፍሬም መሪዎች ጥቂቶቹ የዮሐናን ልጅ ዓዛርያስ፣ የምሺሌሞት ልጅ በራክያ፣ የሰሎም ልጅ ይሒዝቅያ፣ የሐድላይ ልጅ ዓሜሳይ ከጦርነቱ የተመለሱትን በመቃወም፣

13. “እነዚህን ምርኮኞች እዚህ ማምጣት አልነበረባችሁም፤ ያለዚያ እኛ በእግዚአብሔር ፊት በደለኞች እንሆናለን፤ በኀጢአታችንና በበደላችን ላይ ሌላ ልትጨምሩ ታስባላችሁን? በደላችንማ ቀድሞውኑ በዝቶአል፤ ቊጣውም በእስራኤል ላይ ነውና” አሉ።

14. ስለዚህ ወታደሮቹ በሹማምቱና በጉባኤው ሁሉ ፊት ምርኮኞቹን ለቀቁ፤ የተማረከውንም ዕቃ መለሱ።

15. በስም የተጠቀሱ ሰዎችም ምርኮኞቹን ተረክበው ዕራቁታቸውን ለቀሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሷቸው፤ ልብስና ጫማ፣ ምግብና መጠጥ ሰጧቸው፣ በቅባትም ቀቧቸው፤ የደከሙትንም ሁሉ በአህያ ላይ አስቀመጧቸው። ከዚያም ወገኖቻቸው ወደሚገኙባት የዘንባባ ከተማ ተብላ ወደምትጠራው ወደ ኢያሪኮ ወስደዋቸው፣ ወደ ሰማርያ ተመለሱ።

16. በዚያን ጊዜ ንጉሡ አካዝ ወደ አሦር ንጉሥ ልኮ ርዳታ ጠየቀ፤

17. ኤዶማውያን እንደ ገና መጥተው በይሁዳ ላይ አደጋ በመጣል ምርኮኞችን ወስደው ነበርና።

18. ፍልስጥኤማውያን ደግሞ በየኰረብታው ግርጌና በይሁዳ ደቡብ ያሉትን ከተሞች በመውረር ቤትሳሚስን፣ ኤሎንን፣ ግዴሮትን፣ ሦኮን፣ ተምናን፣ ጊምዞንና በአካባቢአቸው የሚገኙትን መንደሮች ሁሉ ያዙ፤ ተቀመጡባቸውም።

19. የእስራኤል ንጉሥ አካዝ ክፋትን በይሁዳ ምድር ስላስ ፋፋና ለእግዚአብሔርም የነበረውን ታማኝነት በከፍተኛ ደረጃ ስላጓደለ፣ እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደ።

20. የአሦር ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር ወደ እርሱ መጥቶ ነበር፤ ሆኖም ችግር ፈጠረበት እንጂ አልረዳውም።

21. አካዝ ከእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከቤተ መንግሥቱና ከመሳፍንቱ ጥቂት ዕቃዎች ወስዶ ለአሦር ንጉሥ ሰጥቶ ነበር፤ ይህም አልረዳውም።

22. ንጉሥ አካዝ በተጨነቀ ጊዜም፣ ለእግዚአብሔር የነበረውን ታማኝነቱን ከምን ጊዜውም ይበልጥ አጓደለ፤

23. እርሱም “የሶርያ ነገሥታት አማልክት እነርሱን ስለ ረዷቸው፣ እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” ሲል እርሱን ላሸነፉት የደማስቆ አማልክት መሥዋዕት አቀረበ።

24. አካዝ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ዕቃዎች ሁሉ አንድ ላይ ሰብስቦ ወሰደ፤ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ በሮች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም በየአውራ ጎዳናው ማዕዘን ላይ መሠዊያ አቆመ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 28