ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 21:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢዮሣፍጥ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮሆራምም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

2. የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ።

3. አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮሆራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና።

4. ኢዮሆራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋር በሰይፍ ገደለ።

5. ኢዮሆራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

6. እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

7. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም የሚጸና መብራት እንዲኖር ለማድረግ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

8. በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 21