ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 21:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ኢዮሣፍጥ እንደ አባቶቹ ሁሉ አንቀላፋ፤ እነርሱ በተቀበሩበትም በዳዊት ከተማ ተቀበረ። ልጁ ኢዮሆራምም በእርሱ ፈንታ ነገሠ።

2. የኢዮሆራም ወንድሞች የሆኑት የኢዮሣፍጥ ልጆችም ዓዛርያስ፣ ይሒኤል፣ ዘካርያስ፣ ዔዛርያስ፣ ሚካኤልና ሰፋጥያስ ይባላሉ። እነዚህ ሁሉ የእስራኤል ንጉሥ የኢዮሣፍጥ ልጆች ነበሩ።

3. አባታቸውም ብዙ የብርና የወርቅ፣ የውድ ዕቃዎችም ስጦታ እንዲሁም በይሁዳ ያሉትን የተመሸጉ ከተሞች ሰጣቸው፤ ነገር ግን መንግሥቱን ለኢዮሆራም ሰጠ፤ የበኵር ልጁ ነበርና።

4. ኢዮሆራም በአባቱ መንግሥት ላይ ተደላድሎ ከተቀመጠ በኋላ ወንድሞቹን በሙሉ ከጥቂት የእስራኤል አለቆች ጋር በሰይፍ ገደለ።

5. ኢዮሆራም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሰላሳ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ስምንት ዓመት ገዛ።

6. እርሱም የአክዓብን ልጅ አግብቶ ስለ ነበር የአክዓብ ቤት እንደ አደረገው ሁሉ የእስራኤል ነገሥታት የሄዱበትን መንገድ ተከተለ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

7. ይሁን እንጂ እግዚአብሔር ከዳዊት ጋር ካደረገው ኪዳን የተነሣ፣ የዳዊትን ቤት ማጥፋት አልፈለገም፤ ለዳዊትና ለዘሩ ለዘላለም የሚጸና መብራት እንዲኖር ለማድረግ ተስፋ ሰጥቶ ነበርና።

8. በኢዮሆራም ዘመነ መንግሥት ኤዶም በይሁዳ ላይ ዐምፆ፣ የራሱን ንጉሥ አነገሠ።

9. ስለዚህ ኢዮሆራም የጦር ሹማምቱና ሰረገላዎቹን ሁሉ ይዞ ወደዚያው ሄደ። ኤዶማውያንም እርሱንና የሰረገላ አዛዦቹን ሁሉ ከበቡ፤ እርሱ ግን በሌሊት ተነሥቶ የከበቧቸውን መታ።

10. ኤዶምም እስከ ዛሬ ድረስ በይሁዳ ላይ እንደ ዐመፀ ነው።ኢዮሆራም የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ስለ ተወ፣ የልብና ከተማ በዚያኑ ጊዜ ዐመፀችበት።

11. ከዚህም በላይ በይሁዳ ኰረብቶች ላይ መስገጃ ስፍራዎች ሠርቶ የኢየሩሳሌም ሕዝብ በዚያ እንዲያመነዝር አደረገ፤ ይሁዳንም አሳተ።

12. ከነቢዩ ከኤልያስ እንዲህ የሚል ደብዳቤ ለኢዮራም መጣ፤“የአባትህ የዳዊት አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘አንተ በአባትህ በኢዮሣፍጥ ወይም በይሁዳ ንጉሥ በአሳ መንገድ አልሄድህም፤

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 21