ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 20:21-32 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

21. ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሠራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣“እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ።

22. መዘመርና ማወደስ እንደ ጀመሩም፣ እግዚአብሔር ይሁዳን በወረሩት በአሞን፣ በሞዓብና በሴይር ተራራ ሰዎች ላይ ድብቅ ጦር አመጣባቸው፤ ተሸነፉም።

23. የአሞንና የሞዓብ ሰዎችም የሴይርን ተራራ ሰዎች ለማጥፋትና ለመደምሰስ ተነሡባቸው። ከሴይር የመጡትን ሰዎች ካጠፉ በኋላም፣ እርስ በርስ ተጠፋፉ።

24. የይሁዳ ሰዎች ምድረ በዳውን ቍልቍል ወደሚያሳየው ቦታ መጥተው ግዙፉን ሰራዊት ሲመለከቱ፣ መሬቱ ሬሳ በሬሳ ሆኖ አዩ፤ አንድም ሰው አላመለጠም።

25. ኢዮሣፍጥና ሰዎቹም ምርኮአቸውን ለማጋዝ ሄዱ፤ በዚያም መካከል እጅግ ብዙ መሣሪያና ልብስ፣ ሊሸከሙ ከሚችሉትም በላይ ውድ ዕቃዎችን አገኙ። ምርኮውም ከመብዛቱ የተነሣ ለመሰብሰብ ሦስት ቀን ፈጀ።

26. በአራተኛውም ቀን እግዚአብሔርን ባመሰገኑበት በበረከት ሸለቆ ተሰበሰቡ፤ ያም ስፍራ እስከ ዛሬ ድረስ የበረከት ሸለቆ ተብሎ የተጠራው ከዚህ የተነሣ ነው።

27. እግዚአብሔር በጠላቶቻቸው ላይ እንዲደሰቱ ስላደረጋቸው፣ የይሁዳና የኢየሩሳሌም ሰዎች ሁሉ በኢዮሣፍጥ እየተመሩ፣ በታላቅ ደስታ ወደ ኢየሩሳሌም ተመለሱ።

28. ወደ ኢየሩሳሌም ከተማ እንደ ገቡም በበገና፣ በመሰንቆና በመለከት ድምፅ ታጅበው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አመሩ።

29. እግዚአብሔር የእስራኤልን ጠላቶች እንዴት እንደተዋጋቸው በሰሙ መንግሥታት ሁሉ ላይ ከእግዚአብሔር ዘንድ ፍርሀት ወደቀባቸው።

30. አምላኩ በየአቅጣጫው ዕረፍት ስለ ሰጠው፣ የኢዮሣፍጥ መንግሥት ሰላም አግኝቶ ነበር።

31. ኢዮሣፍጥ በይሁዳ ላይ ነገሠ። መንገሥ በጀመረ ጊዜም ዕድሜው ሠላሳ አምስት ዓመት ሲሆን፣ በኢየሩሳሌም ተቀሞጦ ሃያ አምስት ዓመት ገዛ። እናቱም የሺልሒ ልጅ ዓዙባ ነበረች።

32. እርሱም በአባቱ በአሳ መንገድ ሄደ፤ ከዚያም ፈቀቅ አላለም፤ በእግዚአብሔርም ፊት መልካም የሆነውን ነገር አደረገ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 20