ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 20:12-21 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

12. አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።

13. የይሁዳ ሰዎች ሁሉ ከሚስቶቻቸው፣ ከልጆቻቸውና ከሕፃኖቻቸው ጋር በእግዚአብሔር ፊት ቆመው ነበር።

14. በዚህ ጊዜ የአሳፍ ዘር በሆነው በሌዋዊው በዘካሪያስ ልጅ፣ በየሕዚኤል ላይ የእግዚአብሔር መንፈስ መጣ። ዘካርያስም የበናያስ ልጅ ሲሆን፣ በናያስም የማታንን ልጅ የሆነው የይዒኤል ልጅ ነው።

15. እርሱም እንዲህ አለ፤ “ንጉሥ ኢዮሣፍጥ፣ እናንተም በይሁዳና በኢየሩሳሌም የምትኖሩ ሁሉ አድምጡ! እግዚአብሔር እንዲህ ይላችኋል፤ ‘ውጊያው የእግዚአብሔር እንጂ የእናንተ አይደለምና፣ ከዚህ ታላቅ ሰራዊት የተነሣ አትፍሩ፣ አትደንግጡ፣

16. ነገ በእነርሱ ላይ ውረዱ፤ እነርሱ በጺጽ መተላለፊያ ሽቅብ ይወጣሉ፣ እናንተም በይሩኤል ምድረ በዳ ውስጥ በሸለቆው መጨረሻ ላይ ታገኟቸዋላችሁ።

17. ይህን ጦርነት የምትዋጉት እናንተ አይደላችሁም፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌም ሆይ፤ ቦታ ቦታችሁን ያዙ፤ ጸንታችሁ ቁሙ፤ እግዚአብሔር የሚሰጣችሁንም ማዳን እዩ። አትፍሩ፤ አትደንግጡም፤ ነገውኑ ውጡና ግጠሙአቸው፤ እግዚአብሔርም ከእናንተ ጋር ይሆናል።’ ”

18. ኢዮሣፍጥ በግምባሩ ወደ መሬት ተደፋ፤ የይሁዳና የኢየሩሳሌምም ሕዝብ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት ወደቁ፤ ሰገዱም።

19. ከቀዓትና ከቆሬ ወገኖች ጥቂት ሌዋውያንም ቆመው፣ እጅግ ከፍ ባለ ድምፅ የእስራኤልን አምላክ እግዚአብሔርን አመሰገኑ።

20. በማግሥቱ ጠዋት በማለዳ ተነሥተው ወደ ቴቁሔ ምድረ በዳ ሄዱ። መንገድ እንደ ጀመሩም ኢዮሣፍጥ ቆሞ፣ “ይሁዳና የኢየሩሳሌም ሕዝብ ሆይ፣ አድምጡኝ! በአምላካችሁ በእግዚአብሔር እመኑ፤ ትጸኑማላችሁ። በነቢያቱም እመኑ፤ ይሳካላችሁማል” አላቸው።

21. ከሕዝቡም ጋር ከተመካከረ በኋላ ከሠራዊቱ ፊት ቀድመው በመሄድ፣“እግዚአብሔርን አመስግኑ፣ ፍቅሩ ለዘላለም ጸንቶ ይኖራልና” እያሉ ለእግዚአብሔር የሚዘምሩና ስለ ቅድስናውም ክብር የሚያወድሱ ሰዎችን መደበ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 20