ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ዜና መዋዕል 20:1-12 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ከዚህ በኋላ ሞዓባውያንና አሞናውያን ከጥቂት ምዑናውያን ጋር ሆነው ኢዮሣፍጥን ለመውጋት መጡ።

2. ሰዎችም መጥተው ኢዮሣፍጥን፣ “ግዙፍ ሰራዊት ሊወጋህ ከሙት ባሕር ወዲያ ካለው ከኤዶም መጥቶብሃል፤ እነሆም፣ ሐሴሶን ታማር በተባለው በዓይንጋዲ ናቸው” አሉት።

3. ኢዮሣፍጥም እጅግ ስለ ፈራ እግዚአብሔርን ለመፈለግ ፊቱን አቀና፤ በይሁዳም ሁሉ ጾም ዐወጀ።

4. የይሁዳ ሕዝብም የእግዚአብሔን ርዳታ ይሻ ዘንድ በአንድነት ተሰበሰበ፤ ከይሁዳ ከተሞች ሁሉም እግዚአብሔርን ለመፈለግ መጡ።

5. ኢዮሣፍጥም በእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ፣ ከአዲሱ አደባባይ ፊት ለፊት በይሁዳና በኢየሩሳሌም ጉባኤ መካከል ቆመ፤

6. እንዲህም አለ፤“የአባቶቻችን አምላክ እግዚአብሔር ሆይ፤ አንተ በሰማይ የምትኖር አምላክ አይደለህምን? የምድር ሕዝቦችን መንግሥታት ሁሉ የምትገዛ አንተ ነህ፤ ኀይልና ሥልጣን በእጅህ ነው፤ ሊቋቋምህም የሚችል ማንም የለም።

7. አምላካችን ሆይ፤ የዚህችን ምድር ነዋሪዎች ከሕዝብህ ከእስራኤል ፊት አሳድደህ ያስወጣህና ለወዳጅህ ለአብርሃም ዘሮች ለዘላለም የሰጠሃቸው አንተ አይደለህምን?

8. እነርሱም ተቀመጡባት፤ ለስምህ መቅደስ ሠሩባት፤ እንዲህም አሉ፤

9. ‘የፍርድ ሰይፍም ሆነ የቸነፈር ወይም የራብ መከራ ቢደርስብን ስምህ በተጠራበት በዚህ ቤተ መቅደስ ፊት ለፊት፣ በፊትህ ቆመን በጭንቀታችን ወደ አንተ እንጮሃለን፤ አንተም ትሰማናለህ፤ ታድነናለህም።’

10. እስራኤል ከግብፅ በወጡ ጊዜ፣ ግዛታቸውን እንዳይወርሩባቸው በማድረግህ ከእነርሱ ተመልሰው ሳያጠፏቸው የቀሩት የአሞን፣ የሞዓብና የሴይር ተራራ ሰዎች እነሆ እዚህ አሉ።

11. እነሆ፣ አንተ ርስት አድርገህ ከሰጠኸን ምድር እኛን በማፈናቀል ወሮታ ሊመልሱልን መጥተዋል።

12. አምላካችን ሆይ፤ አንተ አትፈርድባቸውምን? የመጣብንን ይህን ታላቅ ሰራዊት እንቋቋም ዘንድ አቅም የለንምና የምናደርገውን አናውቅም ነገር ግን ዓይኖቻችን ወዳንተ ናቸው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ዜና መዋዕል 20