ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 9:22-31 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

22. ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ።

23. ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ።

24. ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን በትከሻና ትከሻው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም ዘልቆ ልቡን ስለ ወጋው፣ ሠረገላው ውስጥ ዘፍ ብሎ ወደቀ።

25. ኢዩም የሠረገላ ኀላፊውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፤ “አንሣውና በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ዕርሻ ላይ ጣለው፤ አንተና እኔ አባቱን አክዓብን በየሠረገሎቻችን ሆነን ተከትለነው ስንሄድ፣ እግዚአብሔር ይህን ትንቢት እንዲህ ሲል እንደ ተናገረበት አስታውስ፤

26. ‘ትናንት የናቡቴንና የልጆቹን ደም አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህንንም በዚሁ ዕርሻ ላይ በርግጥ አንተው እንድትከፍል አደርግሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤’ አሁንም በእግዚአብሔር ቃል በተነገረው መሠረት አንሣውና በዚሁ ዕርሻ ውስጥ ጣለው።”

27. የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ይህን ሲያይ፣ ወደ ቤት ሀጋን በሚያወጣው መንገድ ሸሸ፤ ኢዩም እያሳደደ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እርሱንም ግደሉት!” አለ። እነርሱም በይብለዓም ከተማ አጠገብ በጉር ዐቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ውስጥ እንዳለ አቈሰሉት፤ እርሱ ግን ወደ መጊዶ ሸሽቶ፤ እዚያው ሞተ።

28. አገልጋዮቹም በሠረገላ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር በመቃብሩ ቀበሩት።

29. አካዝያስ በይሁዳ የነገሠው፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።

30. ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይኗን ተኳኵላ፣ ጠጒሯንም አሰማምራ በመስኮት ትመለከት ነበር።

31. ኢዩ የቅጥሩን በር አልፎ ሲገባ፣ “ጌታህን የገደልህ አንተ ዘምሪ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ስትል ጠየቀችው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 9