ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 9:16-30 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

16. ከዚያም በሠረገላው ተቀምጦ ወደ ኢይዝራኤል ገሠገሠ፤ ይህን ያደረገውም ኢዮራም በዚያ ስለተኛና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም እርሱን ለመጠየቅ ወደዚያው ስለወረደ ነው።

17. በኢይዝራኤል ግንብ ማማ ላይ የቆመው ጠባቂ የኢዩ ወታደሮች መቅረባቸውን አይቶ፣ “ኧረ ወታደሮች መጡ” በማለት ጮኾ ተናገረ።ኢዮራምም፣ “አንድ ፈረሰኛ ተጠርቶ፤ እንዲገናኛቸው ላኩትና፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎ ይጠይቅ” ሲል አዘዘ።

18. ፈረሰኛውም ኢዩን ለመገናኘት ጋልቦ ሄደና፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ብሎአል” አለው።ኢዩም፣ “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጒዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ እለፍና ተከተለኝ” አለው።ጠባቂውም፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ተመልሶ አልመጣም” ብሎ አሳወቀ።

19. ስለዚህ ንጉሡ ሌላ ፈረሰኛ ላከ፤ ወደ እነርሱ ዘንድ እንደ ደረሰም፣ “ንጉሡ፣ ‘የመጣችሁት በሰላም ነውን?’ ይላል” አለው።ኢዩም “ስለ ሰላም መጨነቅ የአንተ ጒዳይ አይደለም! ይልቅስ ወደ ኋላ እለፍና ተከተለኝ” አለው።

20. ጠባቂው፣ “መልእክተኛው ከእነርሱ ዘንድ ደርሶአል፤ ነገር ግን ይህም ተመልሶ አልመጣም፤ የወታደሮቹ መሪ ሠረገላ አነዳዱ ልክ እንደ ናሜሲ ልጅ እንደ ኢዩ አነዳድ ነው፤ ሲነዳም እንደ እብድ ነው” ሲል አሳወቀ።

21. ኢዮራምም፣ “በሉ ሠረገላዬን አዘጋጁ” ብሎ አዘዘ። ሠረገላው እንደ ተዘጋጀም፣ የእስራኤል ንጉሥ ኢዮራምና የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስ በየሠረገሎቻቸው ሆነው ኢዩን ለመገናኘት ሄዱ፤ የኢይዝራኤላዊው የናቡቴ ርስት በነበረው ዕርሻ ላይም ተገናኙት።

22. ኢዮራምም ኢዩን ገና ሲያየው፣ “ኢዩ፣ የመጣኸው በሰላም ነውን?” ሲል ጠየቀው።ኢዩም፣ “የእናትህ የኤልዛቤል የጣዖት አምልኮና መተት እንዲህ በዝቶ እያለ ምን ሰላም አለ!” ሲል መለሰ።

23. ኢዮራምም ሠረገላውን አዙሮ በመሸሽ፣ “አካዝያስ ሆይ፤ ይህ ክዳት ነው!” አለ።

24. ከዚያም ኢዩ ቀስቱን በማስፈንጠር ኢዮራምን በትከሻና ትከሻው መካከል ወጋው፤ ፍላጻውም ዘልቆ ልቡን ስለ ወጋው፣ ሠረገላው ውስጥ ዘፍ ብሎ ወደቀ።

25. ኢዩም የሠረገላ ኀላፊውን ቢድቃርን እንዲህ አለው፤ “አንሣውና በኢይዝራኤላዊው በናቡቴ ዕርሻ ላይ ጣለው፤ አንተና እኔ አባቱን አክዓብን በየሠረገሎቻችን ሆነን ተከትለነው ስንሄድ፣ እግዚአብሔር ይህን ትንቢት እንዲህ ሲል እንደ ተናገረበት አስታውስ፤

26. ‘ትናንት የናቡቴንና የልጆቹን ደም አይቻለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤ ይህንንም በዚሁ ዕርሻ ላይ በርግጥ አንተው እንድትከፍል አደርግሃለሁ፤ ይላል እግዚአብሔር፤’ አሁንም በእግዚአብሔር ቃል በተነገረው መሠረት አንሣውና በዚሁ ዕርሻ ውስጥ ጣለው።”

27. የይሁዳ ንጉሥ አካዝያስም ይህን ሲያይ፣ ወደ ቤት ሀጋን በሚያወጣው መንገድ ሸሸ፤ ኢዩም እያሳደደ ድምፁን ከፍ አድርጎ፣ “እርሱንም ግደሉት!” አለ። እነርሱም በይብለዓም ከተማ አጠገብ በጉር ዐቀበት መንገድ ላይ በሠረገላው ውስጥ እንዳለ አቈሰሉት፤ እርሱ ግን ወደ መጊዶ ሸሽቶ፤ እዚያው ሞተ።

28. አገልጋዮቹም በሠረገላ አድርገው ወደ ኢየሩሳሌም ወሰዱት፤ በዳዊትም ከተማ ከአባቶቹ ጋር በመቃብሩ ቀበሩት።

29. አካዝያስ በይሁዳ የነገሠው፣ የአክዓብ ልጅ ኢዮራም በነገሠ በዐሥራ አንደኛው ዓመት ነበር።

30. ከዚያም ኢዩ ወደ ኢይዝራኤል ሄደ፤ ኤልዛቤልም ይህን በሰማች ጊዜ ዐይኗን ተኳኵላ፣ ጠጒሯንም አሰማምራ በመስኮት ትመለከት ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 9