ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 9:1-8 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. ነቢዩ ኤልሳዕ ከነቢያት ማኅበር አንዱን ጠርቶ እንዲህ አለው፤ “ወገብህን ታጥቀህ፣ ይህን የዘይት ማሰሮ በመያዝ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሂድ።

2. በዚያም ስትደርስ የናሜሲን የልጅ ልጅ፣ የኢዮ ሣፍጥን ልጅ ኢዩን ፈልገው። ወደ እርሱም ቀርበህ ከጓደኞቹ ለብቻ ከነጠልኸው በኋላ፣ ወደ እልፍኝ አስገባው።

3. ከዚያም ማሰሮውን ይዘህ ዘይቱን በራሱ ላይ አፍስስና፣ ‘እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ “እነሆ፤ እኔ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀባሁህ” ’ ብለህ ዐውጅ። ከዚያም በሩን ከፍተህ ሩጥ፤ ፈጽሞ አትዘግይ።”

4. ስለዚህ ጐልማሳው ነቢይ በሬማት ወደምትገኘው ገለዓድ ሄደ።

5. በዚያ እንደ ደረሰም፣ የሰራዊቱ ጦር መኰንኖች በአንድነት ተቀምጠው ነበር፤ እርሱም “መኰንን ሆይ፤ ወደ አንተ ተልኬአለሁ” አለ።ኢዩም፣ “ለማንኛችን ነው?” ሲል ጠየቀ።እርሱም፣ “መኰንን ሆይ፤ ለአንተ ነው” ብሎ መለሰ።

6. ኢዩም ተነሥቶ ወደ ቤት ገባ፤ ከዚያም ነቢዩ ዘይቱን በኢዩ ላይ አፈሰሰና እንዲህ አለ፤ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፤ ‘በእግዚአብሔር ሕዝብ በእስራኤል ላይ እንድትነግሥ ቀብቼሃለሁ።

7. የአገልጋዮቼን የነቢያትን ደም እንዲሁም የእግዚአብሔርን አገልጋዮች ደም ሁሉ ከኤልዛቤል እጅ እበቀል ዘንድ አንተ የጌታህን የአክዓብን ቤት ትመታለህ።

8. የአክዓብ ቤት በሙሉ ይጠፋል፤ ባሪያም ይሁን ተወላጅ፣ በእስራኤል የሚገኘውን የመጨረሻ ወንድ ልጅ ሁሉ ከአክዓብ እቈርጣለሁ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 9