ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 5:4-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

4. ንዕማንም ወደ ጌታው ሄዶ ከእስራኤል የመጣችው ልጃገረድ ያለችውን ነገረው።

5. የሶርያም ንጉሥ፣ “በል እንግዲያው አሁኑኑ ሂድ፤ እኔም ለእስራኤል ንጉሥ ደብዳቤ እጽፋለሁ” አለው፤ ስለዚህ ንዕማን ዐሥር መክሊት ብር፣ ስድስት ሺህ ሰቅል ወርቅና ዐሥር ሙሉ ልብስ ይዞ ሄደ።

6. ለእስራኤልም ንጉሥ የያዘው ደብዳቤ፣ “ከለምጹ እንድትፈውሰው ይህን ደብዳቤ አስይዤ አገልጋዬን ንዕማንን ወዳንተ ልኬዋለሁ” የሚል ነው።

7. የእስራኤልም ንጉሥ ደብዳቤውን ወዲያው እንዳነበበ ልብሱን ቀዶ፣ “ለምጽ እንድ ፈውሰው ይህን ሰው ወደ እኔ መላኩ እኔ ገድዬ ማዳን የምችል አምላክ ሆኜ ነውን? እንግዲህ ጠብ ሲፈልገኝ እዩ!” አለ።

8. የእግዚአብሔር ሰው ኤልሳዕ፣ የእስራኤል ንጉሥ ልብሱን መቅደዱን በሰማ ጊዜ እንዲህ ሲል ላከበት፤ “ልብስህን ለምን ቀደድህ? ሰውየው ወደ እኔ ይምጣ፤ ከዚያም በእስራኤል ነቢይ መኖሩን ያውቃል።”

9. ስለዚህ ንዕማን በፈረሶቹና በሠረገሎቹ ሆኖ በኤልሳዕ ቤት ደጃፍ ሲደርስ ቆመ።

10. ኤልሳዕም፣ “ሂድና በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ታጠብ፤ ሥጋህ ይፈወሳል፤ አንተም ትነጻለህ” ብሎ እንዲነግረው መልእክተኛ ላከበት።

11. ንዕማን ግን ተቈጥቶ እንዲህ በማለት ሄደ፤ ‘እኔ እኮ በርግጥ ወደ እኔ መጥቶ በመቆም የአምላኩን የእግዚአብሔርን ስም የሚጠራ፣ በእጁም ዳሶ ከለምጽ በሽታዬ የሚፈውሰኝ መስሎኝ ነበር።

12. ለዚህ ለዚህ የደማስቆ ወንዞች አባናና ፋርፋር ከየትኞቹም የእስራኤል ውሆች አይሻሉምን? ለመታጠብ ለመታጠብማ በእነርሱ ታጥቤ መንጻት አልችልምን?” ስለዚህ በቍጣ ተመለሰ።

13. የንዕማን አገልጋዮች ግን ወደ እርሱ ቀርበው፣ “አባት ሆይ፤ ነቢዩ ከዚህ ከበድ ያለ ነገር እንድታደርግ ቢነግርህ ኖሮ አታደርገውም ነበርን? ታዲያ፣ ‘ታጠብና ንጻ’ ቢልህ ምኑ አስቸገረህ?” አሉት።

14. ስለዚህ ንዕማን ወረደ፤ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ነገረውም በዮርዳኖስ ሰባት ጊዜ ብቅ ጥልቅ አለ፤ ሥጋውም እንደ ትንሽ ልጅ ሥጋ ሆነ፤ ነጻም።

15. ከዚያም ንዕማን ከጭፍሮቹ ሁሉ ጋር ወደ እግዚአብሔር ሰው ተመልሶ ሄደ፤ በፊቱም ቆሞ፣ “እነሆ በእስራኤል አገር እንጂ በዓለም ሁሉ ሌላ አምላክ አለመኖሩን ተረድቻለሁ፤ ስለዚህ አሁንም ከአገልጋይህ ስጦታ እንድትቀበል እለምንሃለሁ” አለው።

16. ነቢዩም፣ “የማገለግለውን ሕያው እግዚአብሔርን፣ ምንም ነገር አልቀበልም” ሲል መለሰ። ምንም እንኳ ንዕማን አስጨንቆ ቢለምነውም አልተቀበለም።

17. ንዕማንም እንዲህ አለው፤ “ስጦታውን የማትቀበል ከሆነ፣ ለማንኛውም አምላክ የሚቃጠል ወይም ሌላ መሥዋዕት ስለማላቀርብ፣ ሁለት የበቅሎ ጭነት ዐፈር እንድወስድ ትፈቅድልኝ ዘንድ እለምንሃለሁ።

18. ነገር ግን እግዚአብሔር ስለ አንድ ነገር ብቻ አገልጋይህን ይቅር ይበለው፤ ይኸውም ጌታዬ ለመስገድ ወደ ሬሞን ቤተ ጣዖት በሚገባበት ጊዜ ክንዴን ሲደገፍ እኔም እንደ እርሱ በዚያ ብሰግድ፣ በሬሞን ቤተ ጣዖት በመስገዴ እግዚአብሔር አገልጋይህን ይቅር ይበለው።”

19. ኤልሳዕም፣ “በሰላም ሂድ” አለው። ንዕማን ጥቂት ራቅ ብሎ እንደሄደ፣

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 5