ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 21:6-19 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

6. የገዛ ልጁን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርጎ አቀረበ፤ መተተኛና ጠንቋይ ሆነ፤ ሙታን አነጋጋሪዎችንና መናፍስት ጠሪዎችን ምክር ጠየቀ፤ እግዚአብሔርን ለቊጣ የሚያነሣሣውን ክፉ ድርጊት በፊቱ ፈጸመ።

7. የሠራውን የአሼራን የተቀረጸ ምስል ዐምድ ወስዶ በቤተ መቅደሱ ውስጥ አስቀመጠ፤ ይህም እግዚአብሔር ለዳዊትና ለልጁ ለሰሎሞን፣ “በዚህ ቤተ መቅደስና ከእስራኤል ነገዶች ሁሉ በመረጥኋት በኢየሩሳሌም ስሜን ለዘላለም አኖራለሁ” ያለው ስፍራ ነው።

8. እንዲሁም፤ “ብቻ ያዘዝኋቸውን ሁሉ ተጠንቅቀው በመፈጸምና ባሪያዬ ሙሴ የሰጣቸውንም ሕግ በሙሉ በመጠበቅ ይጽኑ እንጂ ከእንግዲህ የእስራኤላውያን እግር፣ ለአባቶቻቸው ከሰጠኋቸው ምድር ወጥቶ እንዲንከራተት አላደርግም” ያለው ስለ ዚሁ ስፍራ ነው።

9. ሕዝቡ ግን አልሰሙም፤ እግዚአብሔር በእስራኤላውያን ፊት ካጠፋቸው አሕዛብ ይልቅ ክፉ ድርጊት እንዲፈጽሙ ምናሴ አሳታቸው።

10. እግዚአብሔር በባሪያዎቹ በነቢያት አማካይነት እንዲህ ሲል ተናገረ፤

11. “የይሁዳ ንጉሥ ምናሴ ይህን ሁሉ አስጸያፊ ኀጢአት ሠርቶአል፤ ከእርሱ በፊት ከነበሩት አሞራውያን ይልቅ ክፉ ድርጊት ፈጽሞአል፤ ይሁዳንም በጣዖታቱ አስቶአል።

12. ስለዚህ የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር የሚለው ይህ ነው፤ ‘ለሚሰማ ሁሉ ጆሮዎቹ ጭው እንዲሉ የሚያደርግ ክፉ መከራ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ ላይ አመጣለሁ።

13. በሰማርያ ላይ ያዘጋጀሁትን መለኪያ ገመድ፣ የአክዓብንም ቤት የለካሁበትን ቱንቢ በኢየሩሳሌም ላይ እዘረጋለሁ፤ አንድ ሰው ሳሕን እንደ ሚወለውል ከወለወለም በኋላ እንደሚገለብጠው እኔም ኢየሩሳሌምን ወልውዬ እገለብጣታለሁ።

14. የርስቴንም ቅሬታ እተዋቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ ለጠላቶቻቸውም ሁሉ ብዝበዛና ምርኮ ይሆናሉ።

15. ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙና ለቊጣ ስላነሣሡኝ ነው።”

16. ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17. በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

18. ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

19. አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 21