ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 21:15-26 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

15. ይህን የማደርገውም የቀድሞ አባቶቻቸው ከግብፅ ምድር ከወጡበት ጊዜ አንሥቶ እስከ ዛሬ ድረስ በፊቴ ክፉ ድርጊት ስለፈጸሙና ለቊጣ ስላነሣሡኝ ነው።”

16. ይልቁንም ምናሴ፣ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት እንዲፈጽም ይሁዳን ካሳተበት ኀጢአት ሌላ፣ ኢየሩሳሌምን ከዳር እስከ ዳር እስኪሞላት ድረስ ብዙ ንጹሕ ደም አፈሰሰ።

17. በምናሴ ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የሠራውን ኀጢአት ጨምሮ የፈጸመው ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

18. ምናሴም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ “የዖዛ አትክልት” በሚባለው በቤተ መንግሥቱ አትክልት ውስጥ ተቀበረ። ልጁ አሞንም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

19. አሞን ሲነግሥ ዕድሜው ሃያ ሁለት ዓመት ነበር፤ በኢየሩሳሌም ተቀምጦም ሁለት ዓመት ገዛ፤ እናቱ ሜሶላም ትባላለች፤ እርሷም የዮጥባ አገር ሰው የሐሩስ ልጅ ነበረች።

20. አባቱ ምናሴ እንዳደረገው ሁሉ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ድርጊት ፈጸመ።

21. አባቱ በሄደበት መንገድ ሁሉ ሄደ፤ አባቱ ያመለካቸውን አማልክት አመለከ፤ ሰገደላቸውም።

22. የአባቶቹን አምላክ እግዚአብሔርን ተወ፤ በእግዚአብሔርም መንገድ አልሄደም።

23. የአሞንም ሹማምት ዐመፁ፤ ንጉሡንም በቤተ መንግሥቱ ውስጥ ገደሉት።

24. ከዚያም የአገሩ ሕዝብ በንጉሥ አሞን ላይ ያመፁትን ሁሉ ገደሉ፤ ልጁን ኢዮስያስንም በእግሩ ተክተው አነገሡት።

25. በአሞን ዘመነ መንግሥት የተከናወነው ሌላው ሥራ፣ የፈጸመውም ድርጊት ሁሉ በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ ተጽፎ የሚገኝ አይደለምን?

26. እርሱም በዖዛ አትክልት ውስጥ ባለው መቃብሩ ተቀበረ፤ ልጁ ኢዮስያስም በእግሩ ተተክቶ ነገሠ።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 21