ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 2:1-10 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

1. እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ሲደርስ፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልገላ ተነሥተው ይጓዙ ነበር።

2. ኤልያስም ኤልሳዕን፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ቤቴል ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።ኤልሳዕ ግን፣ “ሕያው፣ እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ ካንተ አልለይም” አለው። ስለዚህ አብረው ወደ ቤቴል ወረዱ።

3. በቤቴል የነበሩ የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው አውቀሃልን?” አሉት።ኤልሳዕም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” አለ።

4. ከዚያም ኤልያስ፣ “ኤልሳዕ ሆይ፤ እግዚአብሔር እኔን ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና አንተ በዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፤ “ሕያው እግዚአብሔርን፣ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ።

5. በኢያሪኮ የነበሩትም የነቢያት ማኅበር ወደ ኤልሳዕ ወጥተው፣ “ለመሆኑ እግዚአብሔር፣ ጌታህን ኤልያስን ዛሬ ከአንተ ነጥሎ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት።እርሱም፣ “አዎን ዐውቄአለሁ፤ እናንተ ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰ።

6. ከዚያም ኤልያስ፣ “እግዚአብሔር እኔን ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና አንተ እዚሁ ቈይ” አለው።እርሱም፣ “ሕያው እግዚአብሔርን፤ በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰ። ስለዚህ ሁለቱም አብረው ሄዱ።

7. ከነቢያትም ማኅበር አምሳው ሄደው፣ ኤልያስና ኤልሳዕ ከቆሙበት ከዮርዳኖስ ትይዩ ራቅ ብለው ቆሙ።

8. ኤልያስም ካባውን አውልቆ ጠቀለለውና ውሃውን መታበት፤ ከዚያም ውሃው ግራና ቀኝ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ምድር ተሻገሩ።

9. ከተሻገሩ በኋላም ኤልያስ ኤልሳዕን፤ “ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን ላደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው።ኤልሳዕም፣ “መንፈስህ በዕጥፍ እንዲያድ ርብኝ እለምንሃለሁ” ብሎ መለሰ።

10. ኤልያስም፣ “አስቸጋሪ ነገር ጠይቀሃል፤ ይሁን እንጂ እኔ ከአንተ ስወሰድ ብታየኝ፣ እንዳልከው ይሆንልሃል፤ ያለበለዚያ ግን አይሆንም” አለው።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 2