ብሉይ ኪዳን

አዲስ ኪዳን

2 ነገሥት 17:26-33 መጽሐፍ ቅዱስ፥ አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)

26. ለአሦርም ንጉሥ፣ “ወደ ሰማርያ ከተሞች ወስደህ ያሰፈርኸው ሕዝብ የዚያ አገር አምላክ የሚፈልገውን አላወቀም፤ ከዚህም የተነሣ እግዚአብሔር ሰብሮ የሚገድል አንበሳ ላከበት” የሚል ወሬ ደረሰው።

27. ከዚያም የአሦር ንጉሥ፣ “ከሰማርያ ማርካችሁ ካመጣችኋቸው ካህናት አንዱን፣ በእዚያው እንዲኖር መልሳችሁ ውሰዱትና የአገሩ አምላክ ምን እንደሚፈልግ ሕዝቡን ያስተምር” ሲል አዘዘ።

28. ስለዚህ ከሰማርያ ማርከው ከወሰዷቸው ካህናት አንዱ ወደ ቤቴል ተመልሶ እግዚአብሔርን እንዴት ማምለክ እንደሚገባቸው አስተማራቸው።

29. ያም ሆኖ ግን እያንዳንዱ ወገን በየሰፈረበት ከተማ የራሱን አምላክ ሠራ፤ ያንንም ቀድሞ የሰማርያ ሕዝብ በኰረብታው ላይ በሠራው ማምለኪያ እየወሰደ አቆመ።

30. ከባቢሎን የመጡት ሱኮትበኖትን፣ ከኩታ የመጡት ኔርጋልን፣ ከሐማት የመጡት አስማትን ሠሩ፤

31. አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅ የተባሉትን አማልክት ሲሠሩ፣ ከሴፈርዋይም የመጡት ደግሞ አድራሜሌክና አናሜሌክ ለተባሉት አማልክታቸው ልጆቻቸውን የሚቃጠል መሥዋዕት አድርገው አቀረቡ።

32. እግዚአብሔርን አመለኩ፤ ይሁን እንጂ እያንዳንዱ ወገን የመጣበትን ሕዝብ ልማድ ተከትሎ፣ በየኰረብታው ባሉት ቤተ ጣዖታት የሚያገለግሉትን ካህናት ሾመ።

33. በአንድ በኩል እግዚአብሔርን ሲያመልኩ፣ በሌላ በኩል ግን እንደየአገራቸው ልማድ የየራሳቸውን አማልክት ያመልኩ ነበር።

ሙሉ ምዕራፍ ማንበብ 2 ነገሥት 17